አንጋፋውን ክለብ ለስኬት ያበቃው ሰው

አንጋፋውን ክለብ ለስኬት ያበቃው ሰው

በመጨረሻዎቹ ስድስት የውድድር ዓመታት ሦስት የሊግ ዋንጫዎች!

16 ዓመታት ወደ ኋላ እንመለስ 2001 ዓ.ም፤ ገብረመድኅን ኃይሌ በአሰልጣኝነት ሞያ አስራ አንደኛ ዓመቱ ላይ ነበር። አስደናቂው የእግር ኳስ ሕይወቱን በእርሻ ሰብል አጠናቆ፤ ሁለት ዓመታት በፅሕፈት ቤት ስራ ላይ አሳልፎ፤  ‘ለቤት ምኽሪ ከተማ መቐለ እግር ኳስ ክለብ’ እንዲሁም ትራንስ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ባንኮች ካሰለጠነ በኋላ በተጠቀሰው ዓመት ኢትዮጵያ መድንን ለማሰልጠን ተስማማ።

በአሰልጣኝነት ሕይወቱ የመጀመርያ አስራ አንድ ዓመታት ላይ በተጫዋችነት ዕድሜው ደጋግሞ ካሳካው የሊግ ዋንጫ ጋር የተራራቀው ‘ገብሬ’ በ2001 የውድድር ዓመት ሚካኤል ደስታ እና አብርሃም ይስሃቅን ጨምሮ በርከት ያሉ ዝውውሮች ፈፅሞ፤ ጥሩ እግር ኳስ የሚጫወት ቡድን ገንብቶ ለሊጉ ክብር ቢጠበቅም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ የውድድር ዓመቱን በ30 ነጥብ 9ኛ ሆኖ አጠናቀቀ፤ ከክለቡ ጋርም ተለያየ።

‘Fast Forward’ 2015

መስከረም 5፡ 2015 ዕለተ ሐሙስ፡ ገብረመድኅን ኃይሌ እና ኢትዮጵያ መድን ዳግም የተጣመሩበት ቀን ነበር። ከ14 ዓመታት በፊት መድንን ሲረከብ የሊግ ቻምፒዮንነት ታሪክ ያልነበረው ገብረመድኅን ዳግም ወደ ክለቡ ሲመለስ ግን ከሁለት ቡድኖች ጋር የሊጉን ክብር በማንሳት  የዋንጫ ወዳጅ ሆኖ ነበር የተመለሰው። ሆኖም ጋብቻው ብዙ ውግዘትን አስከተለ ፤ ይባስ ብሎ ቡድኑ በመጀመርያው የሊግ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አስከፊ ሽንፈት በቀመሰበት ወቅት አሰልጣኙ ብሎም ክለቡ ላይ የማያባራ የትችት ናዳ ወረደ። ሆኖም በብዙ ተቃውሞ በጀመረው  የውድድር ዓመት ላይ በ49 ነጥብ 3ኛ ደረጃ በመያዝ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰውን ክለብ ከቀደመው የውጣ ውረድ ጉዞው አላቆ ለዋንጫ ተፎካካሪነት አበቃው።

2017፡ በስድስት የውድድር ዓመታት 3ኛ ዋንጫ !

በ2016 ሁለት መልክ ያለው ዓመት ያሳለፉት ኢትዮጵያ መድን እና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ደካማ አጀማመራቸውን በሁለተኛው ዙር ውጤታማ ጉዞ ማካካስ ቢችሉም በ2015 የውድድር ዓመት ካስመዘገቡት ድምር ነጥብ በአስር ያነሰ በመሰብሰብ ዓመቱን 10ኛ ደረጃ ላይ ሆነው ያጠናቀቁበት ነበር። መድን የ2017 የውድድር ዓመት እስከ 5ኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ድል ሳያደርግ እና በአራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 12 ነጥብ ውስጥ 3ቱን ብቻ በማሳካት ዓመቱን ጀመረ። ቡድኑ ከብዙዎች ግምት ውጭ ቀዝቃዛ አጀማመር ማድረግ ቢችልም ከዛ በኋላ በተከናወኑ ጨዋታዎች ተከታታይ ድሎች እያስመዘገበ መሪነቱ ከተረከበበት 15ኛ ሳምንት ጀምሮ ከሊጉ አናት ሳይወርድ የሊጉን ክብር ማሳካት ችሏል።

መድን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ክብር ባሳካበት እንዲሁም ከ23 ዓመታት በኋላ ከዋንጫ ጋር በታረቀበት፤ ገብረመድኅን ኃይሌ ደግሞ ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳበት ዓመት ላይ ቡድኑ ምንም እንኳን ዘለግ ላሉ ሳምንታት መሪነቱን ተቆናጦ ቢዘልቅም የውድድር ዓመት ጉዞው ግን በፈተናዎች የተሞላ ነበር። በሌሎች የሊጉ ክለቦች ካጋጠመው የወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት በተጨማሪ 8ኛው ሳምንት ላይ ጋቶች ፓኖምን ለኢራቁ ኒውሮዝ አሳልፎ ሰጠ፤ የመጀመርያው ዙር የቡድኑ አምበል እና ወሳኝ ተጫዋች የነበረው ሚሊዮን ሰለሞን እና ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ባልታወቀ ምክንያት ከቡድኑ ተለይተው ወደ አሜሪካ አቀኑ ምክትል አሰልጣኙ ዶክተር ለይኩን ታደሰም በተመሳሳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ አመሩ፤ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እና በወጣቶችና ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረው ቡድን ግን የሊጉን ክብር ከማንሳት ያገዳቸው የለም።

ሐምሌ 28፡ 2012 ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ በተጫዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት ዘመኑ አብዶ መስራት፣ ግብ ማስቆጠርም፣ ሆነ ዋንጫ ማንሳት በግል ከሚሰጠው ደስታ በተጨማሪ ደጋፊዎች ማዝናናትና ማስደሰት ፍፁም እርካታ እንደሚያጎናፅፈው ገልፆ የነበረው አሰልጣኝ ገብረመድኅን በ2010 እና 2011 የጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ከዋንጫ ጋር ካወዳጀ በኋላ ዘንድሮ ደግሞ በክለባቸው የውጣ ውረድ ጉዞ ለተመናመኑ ታማኝ የኢትዮጵያ መድን ደጋፊዎች የዓመታት ልፋታቸው፤ ለታሪካዊው ክለብ ደግሞ በታሪኩ የመጀመርያ የሆነው የሊግ ዋንጫ አበርክቷል።

በሀገራችን እግርኳስ በሰባዎቹ እና ሰማንያዎቹ ከታዩ ከዋክብት አንዱ የሆነው ገብረመድኅን ኃይሌ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአስር ዓመት ቆይታው በርካታ ዋንጫዎች እና የግል ክብሮች አሳክቷል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ዘጠኝ ዓመታት ተጫውቶ ለሰባት ዓመታት ቡድኑን በአምበልነት በመምራት አይረሴው የ1980 የሴካፋ ዋንጫን አንስቷል። ከ1989 በጀመረው የአሰልጣኝነት ሕይወቱም በአፍላነት ዕድሜው በተጫዋችነት ደጋግሞ ያነሳውን ዋንጫ ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር በማንሳት ስሙ ከሀገሪቱ የምንጊዜም ውጤታማ አሰልጣኞች መፃፍ ችሏል።