ያለፉትን ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ቤት ስኬታማ ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በቀጣይ ቆይታቸው ዙርያ ንግግር አድርገዋል።
በ2015 የአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ምክትል በመሆን በኢትዮጵያ ቡና ስራቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ከአንድ ዓመት በኋላ የክለቡ ቦርድ በሀገር ውስጥ አሰልጣኞች “ያለኝ ዕምነት ተሸርሽሯል” በሚል ፊቱን ወደ ውጭ ሀገር አሰልጣኝ በማዞር በዋና አሰልጣኝነት ሰርቢያዊው ኒኮላ ካቫዞቪች እንዲሁም በአካል ብቃት አሰልጣኝነት ሰርቢያዊው ማርኮ ቭላስቪች እንዲይዙት ተደርጎ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በዛው በምክትልነት እንዲቀጥል መደረጉ ይታወሳል።
ሆኖም አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች ለአምስት ወራት ቡድኑን ለቅድመ ውድድር ከማዘጋጀት አንስቶ በሊጉ የስምንት ሳምንት ጉዞ ካደረጉ በኋላ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተከትሎ ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን አይዘነጋም።
አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬም ቡድኑን በኃላፊነት በመረከብ የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቁ ሲሆን በዚህ ቆይታቸውም የኢትዮጵያ ዋንጫን ለክለቡ ማስገኘት ችለዋል። በዚህ መነሻነት የዘንድሮ የውድድር ዓመትን ከቡድኑ ጋር በዋና አሰልጣኝነት የዘለቁት አሰልጣኙ በርካታ ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾችን ከቡድኑ መለያየታቸውን ተከትሎ ቡድኑ አስከፊ የውድድር ዓመት ያሳልፋል ቢባልም ግምቶችን ፉርሽ በማድረግ በአዲስ መልክ ቡድኑን አዋቅረው ጥሩ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ቡድኑ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ አስችለውታል።
አሰልጣኝ ነፃነት ውላቸው ሰኔ ሠላሳ ትናንት መጠናቀቁን ተከትሎ በቀጣይ ቆይታቸው ዙርያ ከቡድኑ ጋር ይቆያሉ ወይስ ? ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ አድርጎታል። በዚህ መነሻነት ክለቡ አሰልጣኝ ነፃነትን ለተጨማሪ ዓመት ለማቆየት ባለው ፍላጎት ትናንት ከክለቡ ስራ አስኪያጅ ጋር ንግግር ማድረጋቸውን አውቀናል።
የመጀመርያ ዙር ንግግራቸውም ከክፍያ ጋር በተያያዘ አሰልጣኙ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም አሰልጣኝ ነፃነት ክለቡ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ያሰበልኝ ካለ እርሱን ብሰማ ይሻለኛል በሚል ተነጋግረው የተለያዩ ሲሆን በቀጣይ ዓርብ ግን የክለቡ ቦርድ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ የድርድሩ ጉዳይ በስፋት እንደሚነሳ እና አሰልጣኙ የመቆየታቸው ነገር ከዕልባት እደሚደርስ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።