አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ፋሲል ከነማ ሊለያዩ ተቃርበዋል

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ፋሲል ከነማ ሊለያዩ ተቃርበዋል

ያለፉትን ሁለት ዓመታት በዐፄዎቹ ቤት ቆይታን ያደረጉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከፋሲል ከነማ ጋር የመለያየታቸው ነገር መቃረቡ ታውቋል።

በ2015 ወርሀ ክረምት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የነበራቸውን ውል ከቋጩ በኋላ የቀድሞ ክለባቸውን ፋሲል ከነማን በመቀላቀል ላለፉት ሁለት ዓመታት በክለቡ ያሳለፉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአፄዎቹ ጋር መለያየታቸውን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ከፋሲል ከነማ ጋር የሦስት ዓመታት ውልን በመፈራረም ሁለቱን ዓመታት ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኙ በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከክለቡ ጋር አስቸጋሪ ጊዜያት አሳልፈው ቢያገባድዱም ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ስለነበራቸው በቀጣዩ ዘመንም ከአፄዎቹ ጋር እንደሚያሳልፉ ከክለቡ ቦርድ ጋር ባደረጉት ንግግር እንደሚቆዮ ቢጠበቅም ቀሪ የውል ዘመን እያላቸው መለያየት ስለመቻላቸው ዝግጅት ክፍላችን አረጋግጣለች። በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ የሚገኙት አሰልጣኙ በዛሬው ዕለት ከክለቡ ጋር በሚለያዩበት ጉዳይ ላይ በወኪላቸው አማካኝነት ከስምምነት የደረሱ መሆኑ ሲታወቅ በቀጣይ ቀናት ሁሉ ነገር እንደሚያልቅ እና አሰልጣኙ ከአሜሪካ ቆይታ መልስ ከአዲስ ክለብ ጋር ሊነጋገሩ እንደሚችሉም ተሰምቷል።