የክለቦች ክፍያ ስርዓት ቀሪ ምርመራዎች ጋር በተያያዘ ታግዶ እንዲቆይ የተደረገው የተጫዋቾች ዝውውር መቼ ሊከፈት እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ፍንጭ አግኝታለች።
የ2017 የውድድር ዘመን በብዙ መለኪያዎች ፈታኝ እና በክስተት የተሞሉ ክንውኖች ተካሂደውበት መጠናቀቁ ይታወቃል። ሁሉም ክለቦች አምነውበት በሙሉ ድምፅ ያፀደቁት የክለቦች የፋይናስ ስርዓት አስተዳደር መመርያን ሦስቱ ክለቦች በመተላለፍ እግድ እንደተጣለባቸው እና ያስመዘገቡት ውጤት በፎርፌ እንዲሸነፉ መደረጉ ይታወሳል።
እንዲሁም የ14 ክለቦችን የፋይናንስ ስርዓት መርማሪው ኮሚቴ ተጨማሪ ክትትል እና ምርመራ እስኪያደርግ ድረስ ከፕሪሚየር ሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚከናወን የተጨዋቾች ዝውውር እንቅስቃሴ ታግዶ እንዲቆይ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ መወሰኑ አይዘነጋም።
ይህ ውሳኔ ከተላለፈ አንድ ሳምንት ያለፈው መሆኑን እና ክለቦች ለቀጣይ ዓመት በአፍሪካ መድረክ ላለባቸው ተሳትፎ እና ለሀገር ውስጥ ውድድር ቡድናቸውን ከወዲሁ ለማጠናከር በማሰብ ወደ ዝውውሩ ለመግባት መቼ ይከፈታል የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል።
ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የመረጃ ምንጮቿ እንዳጣራችው ከሆነ ባሉበት ክለባቸው ውላቸውን ያጠናቀቁ ተጫዋቾች በዛው ለመቆየት ከስምምነትን የደረሱ ካሉ እና ለማፅደቅ ከፈለጉ በቅርቡ ዝውውሩ እንደሚከፍት ሲሰማ ከክለብ ወደ ክለብ የሚደረገው የተጫዋቾች ዝውውር ግን የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ 14 ክለቦች የፋይናንስ ስርዓቱን መመርያ ተከትለው ስለመሰማራታቸው መርማሪው ኮሚቴ በፍጥነት እንዲያሳውቁ እንደተነገራቸው እና ይህ ውጤት እስኪገለፅ ድረስ ከክለብ ወደ ክለብ የሚደረግ ዝውውር የተወሰኑ ቀናት እንደሚወስድ አውቀናል።