አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጥሪ ካደረጉላቸው ሀያ ሦስት ተጫዋቾች መካከል ሦስት ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አይገኙም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ለሁለተኛ ጊዜ ከአስራ አንድ ቀናኖች በኋላ ወደ አሜሪካ በማምራት ከዲሲ ዩናይትድ ከተባለ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታን ያደርጋል። ለዚህ ጨዋታ ይረዳቸው ዘንድ ባለፈው ሰኞ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሀያ ሦስት ተጫዋቾች ጥሪን በማድረግ ከትላንት ማክሰኞ ጀምሮ ሪፖርት በማድረግ በጁፒተር ሆቴል በመገኘት ዝግጅት እንዲጀምሩ ጥሪ የተደረገ ሲሆን ዛሬ ረፋድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ ሲጀምሩ ሦስት ተጫዋቾች ግን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንደማይገኙ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች። ተጫዋቾቹም ረመዳን የሱፍ፣ አህመድ ሁሴን እና ሱራፌል ዳኛቸው ናቸው።
ረመዳን የሱፍ በአሶሳ የሚገኝ ሲሆን ከአውሮፕላን ትኬት ጋር በተገናኘ እንደዘገየ እና ዛሬ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ሲሰማ የአጥቂው አህመድ ሁሴን ምክንያቱ ምንም እንደሆነ ማወቅ አልቻልንም። አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ግን አሜሪካ ስለሚገኝ ቡድኑ ወደ ስፍራው ሲያመራ ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።
