የኢ/ስ አካዳሚ ያዘጋጀው የስፖርት ባለሙያዎች አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል

የኢ/ስ አካዳሚ ያዘጋጀው የስፖርት ባለሙያዎች አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል

ከመላው የሀገሪቱ ክፍል ለተወጣጡ የስፖርት አሰልጣኞች በጥሩነሽ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።

ምስረታውን በ2006 ዓ.ም ያደረገው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሀገርን በዓለም መድረክ የወከሉ ብዙ ስፖርተኞችን ማፍራት የቻለ ተቋም ሲሆን ከምስረታው ጀምሮ አላማ አድርጎ ከተነሳባቸው ስራዎች ውስጥ ተወዳዳሪ እና ሀገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን በማፍራት ለብሔራዊ ቡድን እና ለክለቦች ብቁ ማድረግ፤ በስፖርቱ ዘርፍ ጥናቶችን በማድረግ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማቅረብ እና በስፖርቱ ስር ላሉ ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት ዋነኛ ተልዕኮ አድርጎ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ተተኪዎችን እያፈራ ይገኛል።

በዛሬው ዕለት በአሰላ ከተማ ከሐምሌ 26-30 ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ የአሰልጣኞች ስልጠና የተጀመረ ሲሆን ስልጠናውም በአምስት የተለያዩ የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣በቮሊቦል፣ በቅርጫት ኳስ እና በወርልድ ቴኳንዶ ከሀገሪቱ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ ለ175 አሰልጣኞች አሰላ በሚገኘው በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠናውን መስጠት ተጀምሯል።

ስልጠናውን በይፋ የከፈቱት የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው ባስተላለፉት መልዕክት “አካዳሚው መንግስት የሰጠውን ሁሉንም ተልዕኮዎች በአግባቡ እየተወጣ ነው። ከዚህም ውስጥ የስፖርት ባለሙያዎች ስልጠና አንዱ ነው። ሀገራችን ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ለስፖርት ባለሙያዎች እና አሰልጣኞች ሳይንሳዊ ስልጠና እንዲያገኙ የማብቂያ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ወሳኝ መሆኑን በተግባር ፈትሸን አረጋግጠናል። በቀጣይ ይህን ስልጠና የወሰዳችሁ አሰልጣኞች ወደ ተግባር በመቀየር ሙያዊ ስነምግባር ያለው አትሌት በማፍራት የዜግነት ግዴታችሁን ከመወጣት በተጨማሪ ከዘርፉ ተጠቃሚ ልትሆኑ ይገባል።” ብለዋል።

በመቀጠልም የአካዳሚው የትምህርት ስልጠና እና ውድድር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ በላይ ባስተላለፉት መልዕክት “አካዳሚው ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል አንዱ በሆነው በስፖርት ሙያተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና በየዓመቱ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የስፖርት ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን” ገልፀዋል፡፡ ስልጠናውም ለቀጣይ አምስት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።