👉 “ያደረግናቸው ጨዋታዎች ጥሩ ግብዓት አግኝተንባቸዋል” አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ

👉 “ያደረግናቸው ጨዋታዎች ጥሩ ግብዓት አግኝተንባቸዋል” አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ

የዋልያዎቹ  አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ብሄራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ዙሪያ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ቀደም ብለን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በዋልያዎቹ የአሜሪካ ጉዞ ዙርያ የሰጡትን ሀሳብ ማቅረባችን ይታወሳል አሁን ደግሞ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በጋዜጣዊ መግለጫው የሰጡትን ሀሳብ ወደ እናንተ ለማድረስ ወደድን።

ከጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች በፊት ሾለ ጉዞው ዓላማ አጭር ማብራርያ የሰጡት አሰልጣኙ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል። “አጭር ቆይታ ቢሆንም በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ መልካም የሚባል ሚዛናዊ የሆነ ነገር ተመልክቻለሁ። አንዱ መልካም ጎን ሜዳ ላይ ያለንን ደካማ እና ጠንካራ ጎን በቀጣይ ከግብፅ ጋር ላለን ጨዋታ ሊረዱን የሚችሉ ነገሮችን መመልከት ነው። እነዛን በተወሰነ መልኩ አይተናል፤ ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴም ጥሩ ነው።”

ሾለ ሁለቱ ጨዋታዎች …?

ከዚህ መሄዳችን በፊት አንድ ጨዋታ አድርገናል። ከ ‘ሾሪ ፖይንት’ ጋር ተጫውተናል፤ ያ ጨዋታ ጥሩ ነገር አሳይቶናል በተወሰነ መልኩ። እንደምታውቁት ካለ ማሳደስ እና ፓስፖርት ጋር ተያይዞ ወደ አስር አስራ አንድ የሚሆኑ ባለፉት ጨዋታዎች የነበሩ ተጫዋቾች አልነበሩም፤ ስለዚህ ያንን ለማየት  ጨዋታ አድርገናል እዛ ላይ ገንቢ የሆኑ ነገሮች አግኝተናል። እሱ ጨዋታ በእኛ ጥያቄ ነው የተዘጋጀው፤ እኔ ለሚመለከተው ጥያቄ አቅርቤ፤ ዝም ብለን ከምንሄድ አንዳንድ ክፍተቶቻችንን ለማየት። ደግሞም ብዙ ገንቢ ነገሮች አግኝተንበታል። እንደምናስበው አይደለም ወጣቶች ቢሆኑም ጥሩ ጥሩ ተስፋ ያላቸው ተጫዋቾች ያሉበት እና ሲጫወቱበት የነበረው መንገድም ጠጣር ነው፤ ጠንካራ ነገር ነው ያየሁት።

እዛም ስንሄድ አቶ ባሕሩ እንደገለፁት ከዲሲ ጋር እንጫወታለን ብለን ነው የሄድነው፤ እዛ ሜዳ ላይ የተወሰኑ በተንቀሳቃሽ ምስል ስከታተላቸው የነበሩ ተጫዋቾችን ተመልክቻለው ሌሎች ወጣት ልጆችም አይቻለሁ። ከዚህኛው ጨዋታም በተመሳሳይ ተምረናል።

ወደ ጨዋታዎች ከመሄዳችን በፊት ራሳችንን ለመፈተሽ ክለቦችንም እንጠቀማለን። የሰራነውን ነገር ለመፈተሽ ክፍተቶችና ድክመቶችን ለማየት እርሰ በራስም ጨዋታ አድርገን ነው የምንሄደው ስለዚ እነዚህ ያደረግናቸው ሁለቱ ጨዋታዎች የሚጠቅሙንን ነገሮች ወስደንበታል። ቀጣይ ከግብፅ ጋር ከምናደርገው ጨዋታ በፊት ከክለቦች ጋርም ጨዋታዎችን እናደርጋለን። ስለዚህ ያደረግናቸው ጨዋታዎች ለእኛ ጥሩ ግብዓት አግኝተንባቸዋል።”