አዳማ ከተማ ከሃያ ዓመት በኋላ የቀድሞ አሰልጣኙን ለመሾም ተስማምቷል

አዳማ ከተማ ከሃያ ዓመት በኋላ የቀድሞ አሰልጣኙን ለመሾም ተስማምቷል

ከአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ጋር በስምምነት የተለያየው አዳማ ከተማ የቀድሞ አሰልጣኙን አዲሱ አለቃ ለማድረግ ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አዳዲስ ፊቶችን በሊጉ በማሳየት ከሚነሱ ጥቂት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ በተለይ ያለፉትን አምስት ዓመታት በፋይናንስ እና መሰል ጉዳዮች በተደጋጋሚ ስሙ እየተነሳ መቆየቱ ይታወሳል። በትላንትናው ዕለት ከቡድኑ ጋር ውል የነበራቸውን አሰልጣኝ አብዲ ቡሊን ጨምሮ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን እንዲሁም ደግሞ ከፕሬዝዳንቱም ጋር በቦርድ ውሳኔዎች መሠረት የተለያየው ክለቡ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ሲያደርግ ጥረት በዛሬው ዕለት ከስምምነት እንዳደረሰው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በዚህም መሠረት በ1997 የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ስዩም ከበደም የቡድኑ አዲሱ አሰልጣኝ ለመሆን  ተቃርበዋል።

የስልጠናውን አለም በ1980ዎቹ አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስን የታችኛው ቡድን የጀመሩት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በመቀጠል የቅዱስ ጊዮርጊስን ዋናውን ቡድን ጨምሮ በ1997 አዳማ ከተማን በመቀጠል ወደ የመን ሊግ በማምራት መስራት የቻሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ፣  ሰበታ ከተማ ፣ መቻል ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡናን በሊጉ ማሰልጠን ችለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ እንዲሁም በቅርቡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታችን በአሰልጣኝነት መምራት የቻሉት አሰልጣኙ ከሃያ ዓመታት በኋላ አዳማ ከተማን ዳግም በዋና አሰልጣኝነት ለመረከብ እንደተስማሙ ዝግጅት ክፍላችን የደረሳት መረጃ አመላክቷል።