ሲዳማ ቡና አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ተስማምቷል

ሲዳማ ቡና አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ተስማምቷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በጊዜያዊ አሰልጣኝ ሲመራ የቆየው ሲዳማ ቡና የቀድሞ ረዳት አሰልጣኙን ዳግም በኃላፊነት ለመሾም መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የ2017 የውድድር ዘመን ሲጀመር በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እየተመሩ በርከት ያሉ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው በመቀላቀል ለዋንጫ ሰፊ ግምት እንዲሰጣቸው የሆኑት ሲዳማ ቡናዎች በሂደት የታሰበው ሳይሆን ዋና አሰልጣኙን በመሸኘት በረዳት አሰልጣኙ አዲሴ ካሳ በጊዜያዊነት እየተመራ በሊጉ ያጣውን ስኬት የኋላ ኋላ የኢትዮጵያ ዋንጫን በማንሳት ቢያሳካውም በስተመጨረሻ ያልተገቡ ተጫዋቾችን አሰልፈሃል ተብሎ ዋንጫውን አጥቶ የተደበላለቀ ስሜት ያለው የውድድር ዓመት በማሳለፍ ማጠናቀቁ ይታወሳል።

ለከርሞ ተጠናክሮ ለመምጣት የክለቡ የበላይ አካላት ስራዎችን መስራት የጀመሩ ሲሆን ትናንት ምሽት ባደረጉት ስብሰባ ለቡድኑ አዲስ ዋና አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን እንዲሆኑ ወስነው ተለያይተዋል። ዛሬ ይህን ዘገባ ባጠናከርንበት ወቅት አሰልጣኝ ያሬድ ባሉበት ሁለቱ አካላት ንግግሮችን በማድረግ አብረው ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል። በቀጣይ ስምምነታቸው በፊርማ የሚታሰር ሲሆን አሰልጣኝ ያሬድም በፍጥነት ወደ ስራቸው እንዲገቡ ተነግሯቸዋል።

አሰልጣኝ ያሬድ ከእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወት በኋላ ወደ ስልጠናው ዓለም በመግባት ታዳጊ ከማሰልጠን ጀምሮ  በከፍተኛ ሊግ የሚገኙትን ደቡብ ፓሊስ ፣ ስልጤ ወራቤ እና ኢኮስኮን ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና ረዳት አሰልጣኝ ሲያገለግሉ ቆይተው ሀድያ ሆሳዕናን በዋና አሰልጣኝነት ከመሩ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ውላቸው እስከ ሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ የጦና ንቦችን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ አሁን ከዚህ ቀደም በረዳት አሰልጣኝነት የሰሩበትን ሲዳማ ቡናን ለማሰልጠን ተስማምተዋል።