ከሳምንት በፊት በአሜሪካ ለዲሲ ዩናይትድ ለመጫወት የሙከራ ዕድል ያገኙት አራቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ስትል ሶከር ኢትዮጵያ አጣርታለች።
በዲሲ ዩናይትድ እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መካከል በተደረገው የሦስት ዓመት ስምምነት መሰረት ዋልያዎቹ ወደ ሀገረ አሜሪካ አምርተው ከሁለት ሳምንት በፊት በአውዲ ፊልድ የወዳጅነት ጨዋታ በማከናወን ኢትዮጵያ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፏ ይታወሳል። በዚህ ጨዋታ ላይም የዲሲ ዩናይትድ መልማዮች የተመለከቷቸው አራት የዋልያዎቹ ተጫዋቾች ከንአን ማርክነህ ፣ ቢንያም በላይ ፣ ሀብታሙ ተከሰተ እና ራምኬል ጄምስ በአሜሪካ MLS እና USL ለመጫወት የሙከራ ዕድል ማግኘታቸው ይታወቃል።
አብዛኛው የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ከሳምንት በፊት ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ አራቱ ተጫዋቾች በቀጣይ ለሚኖራቸው የሙከራ ጊዜ ሲባል በዛው በአሜሪካ ከቀሩ ሁለት ሳምንት ሆኖታል። ታዲያ ሶከር ኢትዮጵያ እነዚህ አራት ተጫዋቾች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ስትል ማጣራት አድርጋ ያገኘችውን መረጃ እንዲህ አቅርባዋለች።
ያረፉበት ሆቴል
አራቱ ተጫዋቾች ማረፊያቸውን ያደረጉት በዲሲ ዩናይትድ በሚገኘው የባለሃብቱ ጆን ማሞ ንብረት በሆነው ሂልተን ሆቴል ሲሆን አስቀድመው ቤልቪየር ሆቴል ነበሩ።
የሙከራ ዕድል የሚያደርጉበት ሜዳ
ካረፉበት ሂልተን ሆቴል የአርባ ደቂቃ የመኪና መንገድ በሚወስደው በሎውደን ዩናይትድ የልምምድ ማዕከል ኢኖቫ ፐርፎርማንስ ኮምፕሌክስ ሜዳ የሙከራ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ይሆናል።
የሙከራ ጊዜያቸው ምን ይመስላል?
ክለቡ ዲሲ ዮናይትድ የሙከራ ጊዜውን በሁለት ዙር በተከፈለ መርሐ-ግብር የሚያከናውን ይሆናል። ይህ ማለት ሁለት ተጫዋቾች ለአንድ ሳምንት ሲታዩ የቀሩት ሁለት ተጫዋቾች አራፊ ሆነው በሌላ ጊዜ የሚታዩ ይሆናል። በዚህም መሰረት ከንዓን ማርክነህ እና ሀብታሙ ተከሰተ የመጀመርያው ዙር ሙከራ አድራጊ ሲሆኑ በመቀጠል ቢንያም በላይ እና ራምኬል ጀምስ በሁለተኛው ዙር ሙከራውን ያከናውናሉ።
የሙከራው አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
በወጣው የሙከራ ሰሌዳ መሰረት ከንአን ማርክነህ እና ሀብታሙ ተከስተ ለአንድ ሳምንት ኢኖቫ ፐርፎርማንስ ኮምፕሌክስ የልምምድ ማዕከል የተሰጣቸውን የሙከራ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ አጠናቀው ጨርሰዋል። አሁን አራፊ ይሆናሉ ማለት ነው።
የተቀሩት ሁለቱ ተጫዋቾች መቼ ሙከራ ያደርጋሉ?
ቢንያም በላይ እና ራምኬል ጀምስ በግላቸው ጠንካራ የዝግጅት ጊዜ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ኢኖቫ ፐርፎርማንስ ኮምፕሌክስ የልምምድ ማዕከል ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን የሙከራ ጊዜ የሚጀምሩ ይሆናል።
ቀጣይ ሁኔታስ?
አራቱም ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነሐሴ ወር መጨረሻ ለሚያደርጋቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑን የሚቀላቀሉ ይሆናል።
የሙከራው ውጤት መቼ ይገለጻል?
አራቱም ተጫዋቾች ያደረጉት ሙከራ የመጨረሻ ውጤት እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ እርግጠኛ ሆኖ በእንደዚህ ቀን ይገለፃል ባይባልም ክለቦቹ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ሙከራውን ያለፉ ተጫዋቾች ውጤት ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዲሲ ዩናይትድ እና ላውደን ዩናይትድ ክለቦች የተጫዋቾቹ ፈላጊዎች መሆናቸው ይታወቃል።