ምዓም አናብስት ተከላካዮቹን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል

ምዓም አናብስት ተከላካዮቹን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል

መቐለ 70 እንደርታዎች ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

ከቀናት በፊት ወደ ዝውውሩ በመግባት ሱሌይማን ሐሚድን ለማስፈረም የተስማሙት በአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የሚመሩት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በስሑል ሽረ ቆይታ የነበራቸውን ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

ቀዳሚው ወደ ቡድኑ ለማቅናት ከስምምነት የደረሰው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ነው። በአንድ ዓመት የስሑል ሽረ ቆይታው በ32 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2812′ ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በጋሞ ጨንቻ፣ ጎፋ ባራንቼ፣ ወሎ ኮምቦልቻ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሃያ ሦስት ዓመት በታች መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ከስሑል ሽረ ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ምዓም አናብስትን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል።

ሁለተኛው ምዓም አናብስትን ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች እንደ አሰጋኸኝ ሁሉ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በስሑል ሽረ ቆይታ የነበረው አብዲ ዋበላ ነው።

በ2017 የጥር የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማን በመልቀቅ ስሑል ሽረን ተቀላቅሎ በውድድር ዓመቱ በሁለቱም ቡድኖች መለያ በድምሩ በ16 ጨዋታዎች ተሳትፎ 1060′ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው በመስመር ተከላካይነት እና በአጥቂ ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ ከአዳማ ከተማ ሁለተኛ ቡድን በኋላ በዋናው ቡድን ደረጃ በአሳዳጊ ክለቡ አዳማ ከተማ እና ስሑል ሽረ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን መጫወቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ያመራ ሁለተኛው ተጫዋች ሆኗል።