ፋሲል ከነማዎች የፊት መስመር ተጫዋቹን ለማስፈረም ተስማምተዋል።
ቀደም ብለው ግብ ጠባቂው ሞየስ ፖዎቲ እና ሁለገቡ ናትናኤል ወልደጊዮርጊስን ለማስፈረም ተስማምተው የግዙፉ ተከላካይ ምኞት ደበበን ውል ለተጨማሪ ዓመት ለማራዘም የተስማሙት ፋሲል ከነማዎች አሁን ደግሞ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በመቐለ 70 እንደርታ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገውን የፊት መስመር ተጫዋቹ ያሬድ ብርሃኑን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
በ2017 የውድድር ዓመት በ29 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2158′ ደቂቃዎች ቡድኑን በማገልገል በውድድር ዓመቱ 10 ግቦች በማስቆጠር ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ተጫዋቹ ስሙ ከበርካታ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ቢቆይም በስተመጨረሻ ዐፄዎቹን ለመቀላቀል ተስማምቶ አመሻሽ ላይ የሕክምና ምርመራውን አጠናቋል። ከዚህ ቀደም በመቐለ 70 እንደርታ፣ ደደቢት፣ ወልዲያ ከተማ፣ ወልዋሎ፣ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀንና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጫወት የቻለው አጥቂው የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንም ማገልገሉ ይታወቃል።