ወላይታ ድቻ እና አል ኢትሃድ ትሪፖሊ ሁለቱም በተመሳሳይ በአዲስ አሰልጣኝ እየተመሩ የሚያደርጉት የኮንፌደሬሽን ዋንጫ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ በነገው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።
በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለው ወላይታ ድቻ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሊቢያው ተወካይ አል ኢትሃድን በመግጠም ውድድሩን ይጀምራል።
ነሐሴ 16 በመቀመጫ ከተማቸው ሶዶ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በመጀመር ወደ አዳማ ከተማ አምርተው ላለፉት 28 ቀናት በዝግጅት ላይ የቆዩት በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት የጦና ንቦቹ በዝውውር መስኮቱ አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርመው የነባሮች ውል ካራዘሙ በኋላ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የልምምድ ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን አዲሱ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራም በነገው ዕለት በሚደረገው ፍልሚያ ለመጀመርያ ጊዜ በነጥብ ጨዋታ ቡድኑን ይመራሉ።
የሊቢያን ፕሪሚየር ሊግ 18 ጊዜ፣ የሊቢያን ዋንጫ 7 ጊዜ፣ የሊቢያ ሱፐር ካፕ 11 ጊዜ እንዲሁም በ2001 የካፍ አሸናፊዎች ዋንጫ ያሸነፈው አል ኢትሀድ በሊብያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ አል አህሊ ቤንጋዚን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ የኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊነቱን በማረጋገጥ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል።
በአህጉረ አፍሪካ ልምድ ያላቸው እና ከዚህ ቀደም ቪያርያል፣ ርያል ቤቲስ፣ ክለብ ብሩዥ፣ አል አህሊ እንዲሁም ራጃ ካዛብላንካ ጨምሮ በርከት ያሉ ክለቦችን ካሰለጠኑት ስፔናዊው አሰልጣኝ ሁዋን ካርሎስ ጋሪዶ በመለያየት አሰልጣኝ ሐምዲ ባተውን የቀጠሩት አል ኢትሀዶች እንደ ወላይታ ድቻ ሁሉ በአዲስ አሰልጣኝ እየተመሩ ወደ ወሳኙ ጨዋታ ይቀርባሉ። አዲሱ አሰልጣኝም ቡድኑን በተረከቡ በ79 ኛው ቀን ላይ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በካፍ ውድድሮች ያላቸው ታሪክ
ወላይታ ድቻዎች በ2017 የውድድር ዓመት ብቸኛው አህጉራዊ ውድድር ተሳትፏቸው ነው። በወቅቱ የታንዛንያውን ዚማሞቶ በማሸነው ወደ አስራ ስድስት ውስጥ ገብተው በቀጣዩ ዙር የግብፁን ዛማሌክ በማሸነፍ በታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ከውድድሩ የወጡበትም የክለቡ ብቸኛው የኮንፌደሬሽን ተሳትፎ ነው።
አል ኢቲሃድ ከዚህ ቀደም በ27 አጋጣሚዎች በካፍ ውድድሮች የተሳተፈ ሲሆን 15 ጊዜያት በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ፤ 11 ጊዜያት በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ እንዲሁም በአንድ አጋጣሚ በ2004 ወደ ካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ በተጠቃለለው ‘African Cup Winners’ Cup’ መሳተፍ ችለዋል። በ2001 በአንጋፋው ውድድር ‘CAF Cup Winners Cups’ ያሸነፉበት እንዲሁም በ2007 በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ በ2010 ደግሞ በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ላይ ግማሽ ፍፃሜ የደረሱበት ደግሞ በክለቡ ታሪክ ምርጡ ውጤታቸው ነው።
ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ ሙሉ ስብስባቸውን ይዘው ጨዋታውን ይጠባበቃሉ። በአል ኢትሃድ በኩል በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪና ወሳኝ ተጫዋች የነበረው ግብፃዊው አሕመድ ካህራባ በቅርቡ ወደ ክዌቱ ቃዳስያ አምርቷል። ሆኖም በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀለው ቶጓዊው ሮጀር አሆሉ እና ሊቢያዊው መሐመድ አል ዘንታኒ ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።