በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ የሊቢያውን አል ኢትሃድን በሜዳው የገጠው ወላይታ ድቻ ጨዋታውን ያለ ግብ ቋጭቷል።
የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል የኢትዮጵያ ተወካይ ወላይታ ድቻ የሊቢያውን ተወካይ አል ኢትሃድን በአዲስ አበበ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አስተናግዷል። እንግዳው ቡድን ጠንከር ብሎ የጨዋታ ብልጫ በወሰደበት በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በተለየም በግራ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ውስጥ በተደጋጋሚ እየገቡ የግብ እድል መፈጠር ችለዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሆነው ጠንካራው ሙከራ ሲታወስ ለትንሽ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ መሪ ሊያደርጋቸው የቀረበ የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራ ነበር።
የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በመከላከሉ ረገድ በአመዛኙ ጥሩ የነበሩት የጦና ንቦች ከረጅም ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገው ዘለግ ካለ ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። 38ኛው ደቂቃ ላይ በከኔዲ ከበደ ላይ በተሰራ ጥፋት የቆመ ኳስ ቴዎድሮስ ታፈሰ አሻምቶ ካርሎስ ዳምጠው ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ሳይጠበቅ ኳሱን ከፍ አድርጎ በግቡ አናት ያሳለፈበት አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል።
በአጋማሹ የግብ እድሎችን በመፈጠር የተሻሉ የነበሩት አል ኢትሃዶች የአጋማሹ መጠናቀቂያ 42ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል ኳስ ይዘው ገብተው አህመድ አልሳፊ ተከላካዮችን አልፎ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያደረገው ሌላኛው ጥራት ያለው ሙከራ ሲጠቀስ የግቡ ቋሚ ብረት ብረት ባይመልስባቸው አጋማሹን እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ያቀረባቸው ሙከራ ሆኖ ነገር ግን አጋማሹ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳው ቡድን ወላይታ ድቻ ከመጀመሪያ አጋማሽ አንፃር ጠንከር ብለው በመመለስ ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን እየገቡ በደጋፊያቸው ፊት ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ወደ መልስ ጨዋታ ለማቅናት ወሳኙን ነጥብ ለማሳካት ሲጥሩ ተመልክተናል። ሆኖም ግን ተጋጣሚው ቡድን ከሜዳው ውጪ በመሆኑ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት በማሰብ ሁለተኛውን አጋማሽ በአማዛኙ ከሜዳቸው ወረድ ብለው መከላከሉ ላይ ያተኮሩበትን አጨዋወት ይዘው በመመለሳቸው ግብ ማስቆጠሩ ቀላል አልሆነላቸውም።
የጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው የጦና ንቦች ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን እንዲሁም አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው የነበሩ ሲሆን ከእነዛ መካከል ያሬድ ዳርዛ 56ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ ይዞ ገብቶ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ከግቡ ቋሚ ብረት ለጥቂት ርቆ ያለፈበት፣ እንዲሁም 77ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ሳችጠቀም የቀረበት ሌላኛው አስቆጪው አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር።
አንዱን ነጥብ ይዘው ለመውጣት መከላከሉ ላይ የተጠመዱት አል ኢትሃዶች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል፤ 64ኛው ደቂቃ ላይ እና 75ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጓቸው አደገኛ ሙከራዎች ሲታወሱ ናኡፍ ዴራሪ ከመልስ ውርወራ የተሻገረውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ጠንከር ያለ ኳስ መጥቶ ቢኒያም ገነቱ በግሩም ሁኔታ አድኖባቸዋል።
ጭማሪ ደቂቃ ላይ ወላይታ ዲቻዎች ጫን ብለው ገብተው ሳጥን ውስጥ ሙከራ ሲያደርጉ ኳስ በእጅ ተነክቷል ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል ጥያቄ ቢያቀርቡም የእለቱ ዳኛ ጨዋታው አስቀጥለው ግብ ሳይቆጠርበት 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።