👉 “ከዛ በላይ ተጭነን ውጤቱን ማስፋት ነበር የፈለግነው።”
👉 “እዛ አስቸጋሪ ሊሆንብን እንደሚችል እገምታለሁ።”
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የካፍ ቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ በአማኑኤል ኤርቦ እና ብሩክ ሙሉጌታ ግቦች ሁለት ለባዶ ካሸነፈ በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል።
ስለ ጨዋታው?
“እቅዳቸን ማሸነፍ ነው። በእቅዳችን መሰረት ማሸነፍ አንድ ነገር ነው ጥሩ ነገር አግኝተናል፤ ግን ከዛ በላይ ተጭነን ውጤቱን ማስፋት ነበር የፈለግነው ግን ሁኔታዎችም አንዳንዴ አይመቹም። ትንሽ የማንሸራተት ነገር ስላመጣ ሜዳው መቆጣጠር ትንሽ አስቸግሯቸዋል ከዛ ውጭ ግን ጥሩ ነው።”
ስለ ተጋጣሚያቸው?
“ጥሩ ነው ቦታቸውን ዘግተው ነው የተጫወቱት፤ ምናልባትም እነሱ የፈለጉት እዚህ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ነበር ሀሳባቸው፤ ግን ባሰቡት መንገድ አልሄደም። እዛ አስቸጋሪ ሊሆንብን እንደሚችል እገምታለሁ።”
ስለ ተጫዋቾቻቸው አካል ብቃት ?
“በእርግጥ ከዕረፍት አይደለም የመጡት፤ የተወሰኑ መቆራረጦች ነበሩብን አንዳንድ ተግዳሮቶች ነበሩብን፤ ግን ከነበርንበት ሁኔታ አንፃር ሲታይ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። ግን ገና በሂደት ውህደት እየፈጠረ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።”
በውድድሩ እስከ ምን ድረስ ሊጓዙ ይችላሉ?
“እንግዲህ አናውቀውም ዛሬ ላይ ሆነን ብዙ ነገር መናገር አንችልም። ገና የመልስ ጨዋታ ገና አለ፤ ከመልሱ ጨዋታ በኋላ ደግሞ እሱን አሸንፈን ከወጣን ከዛ በኋለ የምናየው ይሆናል።”