የኢትዮጵያ መድን አጥቂ አማኑኤል ኤርቦ አሁናዊ የጉዳት ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
በ2025/26 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ኢትዮጵያን የሚወክለው ኢትዮጵያን መድን የዛንዚባር አቻውን ምላንዴጌን ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አስተናግዶ በአማኑኤል ኤርቦ እና በብሩክ ሙሉጌታ ሁለት ጎሎች በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን አስፍቶ መውጣቱ ይታወቃል።
በጨዋታው ላይ ጎል አስቆጣሪው አማኑኤል ኤርቦ እና የምላንዴጉ ግብ ጠባቂ ኳስ በሚሻሙበት ወቅት ተጋጭተው ከበድ ያለ ጉዳት በማስተናገዳቸው እና ለተሻለ ሕክምና ሁለቱም በአምቡላንስ ወደ ግሩም ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልፀን ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ አጥቂው አማኑኤል ኤርቦ በግጭቱ ትከሻው አካባቢ ጉዳቱ እንዳጋጠመው እና ሲቲስካን ተነስቶ የጉዳቱ ሁኔታ የታሰበውን ያህል ከባድ እንዳልሆነ እና ስብራትም ሆነ ውልቃት እንደሌለው ለቀናት ዕረፍት እንዲያደርግ እንደተነገረው ሰምተናል ሆኖም ተጫዋቹ ለመልሱ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።