👉 “በሁለተኛው አጋማሽ ግን ሰርተነው የመጣነው ነገር ለማድረግ ሞክረናል”
👉 “የነበሩብን ክፍተቶች አሻሽለን ቀጣይ በደምብ አጥቅቶ ለመጫወትና ግብ ለማስቆጠር በደምብ ጠንክረን ነው የምንሄደው”
በ2026 በፖላንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ የኬንያ አቻቸውን ያስተናገዱት ትናንሾቹ ሉሲዎች ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ የሰጠው አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ስለ ጨዋታው ?
ጨዋታው ጠንካራ ነበር። ኬንያ እንደሚታወቀው ጠንካራ ቡድን ነው፤ የኛም ጠንካራ ቡድን ነው በደምብ ተጀጋጅተን ነበር የቀረብነው፤ ከፍተኛ ዝናብ ነበር። ይዘነው የመጣነው አጨዋወት ኳሱን ተቆጣጥሮ ማጥቃትና ነጥብ ይዞ መውጣት ነበር።
በእንቅስቃሴ ረገድ በመጀመርያው አጋማሽ ያንን ማድረግ በጣም ተቸግረን ነበር ምክንያቱ ኳሱ እንደፈለግነው መንቀሳቀስ አልቻለም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ሰርተነው የመጣነው ነገር ለማድረግ ሞክረናል ውጤቱም በአቻ አልቋል።
ስለ ቅያሪዎች ?
በመጀመርያው አጋማሽ የነበረው ነገር ተመልክተን በሁለተኛው አጋማሽ እንደገባን ለመቀየር ነበር ያሰብነው ግን ስንመለከተው ጨዋታው እየተሻሻለ ነው የመጣው። ያንን ደግሞ አፍርሶ እንደገና ለመጀመር ምርጥ 11 ውስጥ የገቡትን ተጫዋቾች በደምብ እየቀጠሉ ስለነበሩ ነው እንጂ ከውጭም ያለው ሀይል ጥሩ ነው። ቢዘገይም ከገቡ በኋላ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
ስለ መልስ ጨዋታ ?
በጣም ጠንካራ ቡድን እንደሆነ አይተናል። ‘Press’ የሚያደርጉበት መንገድ ጠንካራ ነው፤ ስለዚ እዛ ስንሄድ ደግሞ የሚዘጋጁበት መንገድ ሌላ ሊሆን ይችላል። እኛ ዛሬ የነበሩብን ክፍተቶች በደምብ አሻሽለን ቀጣይ በደምብ አጥቅቶ ለመጫወት ግብ ለማስቆጠር በደምብ ጠንክረን ነው የምንሄደው።