በአ.አ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች ኤሌክትሪክ ድል ሲቀናው ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በአ.አ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች ኤሌክትሪክ ድል ሲቀናው ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሦስተኛው ሳምንት የምድብ ሁለት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አርባምንጭ ከተማ

የመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር የታየበት ቢሆንም አርባ ምንጭ ከተማዎች ዕድሎች በመፍጠር እንዲሁም ሙከራዎች በማድረግ የተሻሉ ነበሩ። በ 14ኛው ደቂቃም  ኤፍሬም ታምራት ወደ ሳጥኑ ያሻገራትን ኳስ ይገዙ ቦጋለ በማስቆጠር አዞዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
በከግቧ በኋላ ኤሌክትሪኮችም በሀብታሙ ሸዋለም አማካኝነት ከቆመ ኳስ ሙከራ ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም ኳሷ አግዳሚው ለትማ ወደ ውጭ ወጥታለች።

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር እና የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። በ51′ ደቂቃም ሀብታሙ ሽዋለም ከቆመ ኳስ አሻግሯት ኢድሪሱ ኦጎዶጆ ኳሷን ሲቆጣጠር በፈጠረው ስህተት በፍቃዱ አስረሳኸኝ ግብ አስቆጥሮ ኤሌክትሪክን አቻ ማድረግ ችሏል። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም ኤሌክትሪኮች ጨዋታውን የሚመሩበት ግብ አስቆጥረዋል። አብነት ተስፋዬ በረዥሙ የተሻገረችውን ኳስ ተቆጣጥሮ አመቻችቷት ሀሰን ሑሴን በጥሩ አጨራረስ ያስቆጠራት ግብም ኤሌክትሪኮችን መሪ ማድረግ ችላለች። ጨዋታው 76′ ደቂቃ ሲደርስም ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ኢዲሪሱ ኦጎዶጁ ስህተት ሰርቶ የአዞዎቹ ተከላካዮች በአግባቡ ያላራቋት ኳስ አቤል ሀብታሙ አግኝቶ በግሩም ሁኔታ ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት ግብም ኤሌክትሪክ ከኋላ ተነስቶ ሦስት ለአንድ እንዲመራ አስችላለች። በአጋማሹ አርባምንጭ ከተማዎች በርናንድ ኦቼንድ በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች እንዲሁም በታምራት እያሱ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ኳስና መረብ ሳያገናኙ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህርዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የጣና ሞገዶቹ እና ቡናማዎቹ ያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። በአጋማሹ በሁሉም ረገድ ብልጫ የነበራቸው ቡናማዎቹ በጨዋታው ጅማሮ አቡበከር አዳሙ ከመዓዝን ምት በሞክራት እንዲሁም አማኑኤል አድማሱ የተመለሰችውን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው በመለሳት ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ጫና መፍጠራቸው የቀጠሉት ቡናዎች አማኑኤል አድማሱ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል መቷት የግቡን አግዳሚ በመለሳት እንዲሁም ዘላለም አባተ ከመሀል ሜዳ በቀጥታ መቷት ግብ ጠባቂው ጨርፏት አግዳሚውን ገጭታ በተመለሰች ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ብያደርጉም አጋማሹ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

 

ባህርዳር ከተማዎች ውስን መሻሻል ባሳዩበት ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም ጥቂት ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። በባህርዳር ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከረዥም ርቀት ያደረጋት ሙከራ በቡናማዎቹ በኩል ደግሞ በጨዋታው መጠናቀቅያ ደቂቃዎች አማኑኤል አድማሱ ከመስመር የተሻገረችውን ኳስ መቶ ፔፔ ሴይዶ በጥሩ ብቃት ባዳናት ሙከራ ቡድኖቹ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ማድረግ ቢችሉም ጨዋታው ግን ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።