በሀ.ዩ.ስ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች መቻል ድል ሲቀናው ምድረ ገነት ሽረ እና ወልዋሎ ነጥብ ተጋርተዋል

በሀ.ዩ.ስ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች መቻል ድል ሲቀናው ምድረ ገነት ሽረ እና ወልዋሎ ነጥብ ተጋርተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሦስተኛው ሳምንት የምድብ አንድ የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች መቻል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲረታ የምድረ ገነት ሽረ እና ወልዋሎ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ።

ምድረገነት ሽረ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ቀዝቃዛ እንዲሁም የግብ ዕድሎችም ሆነ ሙከራዎች ያልተደረጉበት የመጀመርያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ ወልዋሎዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም በቢጫዎቹ ረገድ ኪሩቤል ወንድሙ ከቅጣት ምት ቀጥታ መቷት የግቡን አግዳሚ ለትማ ከተመለሰች እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግ አጋማሹ ተጠናቋል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ማራኪ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በረዣዥም እንዲሁም በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ግን ጥቂት ነበሩ። ሽመክት ጉግሳ የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ኳሷን ለማራቅ ሲሞክር በፈጠረው ስህተት ያገኛትን ኳስ መቶ ከግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣችው ሙከራም ሽረ ምድረ ገነትን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። ጥቂት ሙከራ እንዲሁም ሳቢ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ጨዋታም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

መቻል ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሁሉም ረገድ መቻል ብልጫ በወሰደበት አጋማሽ ጦሩ ኳስን ተቆጣጥሮ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረገበት ሲሆን በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎችም በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችሏል፤ በተለይም ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። በ38ኛው ደቂቃ ግን ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ መስመር አሻግሯት መሐመድ አበራ ከመረቡ ጋር ባዋሀዳት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በ40ኛው ደቂቃም አለምብርሀን ይግዛው ከቸርነት ጉግሳ የተቀበላትን ኳስ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ የመቻልን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ በተወሰነ መልኩ ተመጣጣኝ በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ቢፈጥሩም ወደ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ጥቂት ናቸው። በ57 ኛው ደቂቃም ዳዊት ማሞ ከቀኝ መስመር አሻግሯት መሐመድ አበራ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደሞ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሯል። ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ የቆዩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችም በ78ኛው ደቂቃ በሳይመን ፒተር አማካኝነት ከፍፁም ቅጣት ምት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ጨዋታው ሊገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩትም አብዱልከሪም ወርቁ ያደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ የጦሩን መሪነት ለማስፋት የተቃረበች ስትሆን ጥሩ እንቅስቃሴ እና አራት ግቦች ያስመለከተው ጨዋታም በመቻል አሸናፊነት ተጠናቋል።