የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ : የሶከር ኢትዮጵያ የህዳር / ታህሳስ ወር ምርጦች

ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ፐሪሚየር ሊግ የወሩ ኮከቦችን ለመጀመርያ ጊዜ የመረጠችው የሶከር ኢትዮጵያ የ2ኛውን ወር ኮከቦች ጊዜውን ጠብቃ መርጣለች፡፡ ባለፈው ወር ከተካተቱት ተጫዋቾች መካከል አንድም ተጫዋች በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት የቀረ ሲሆን ከአንዳንዶቹ ውጪ አብዛኛዎቸ ተጫዋቾች በዚህኛው ወር ደካማ አቋም ማሳየታቸው የሊጉ ተጫዋቾች ወጥ አቋም የማሳየት ችግር ያመላከተ ሆኗል፡፡

በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያ ቡና 4 ተጫዋቾችን በማስመረጥ ቀዳሚ ሲሆን መብራት ኃይል እና ወላይታ ድቻ እያንዳንዳቸው ሁለት አስመርጠዋል፡፡

ከህዳር 16 እስከ ታህሳስ 16 ድረስ የተካሄዱ የአራት ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ ያሳዩትን አቋም ተመርኩዞ የተደረገው ምርጫ ይህንን ይመስላል፡፡

የህዳር / ታህሳስ ወር 11 ምርጦች (4-3-3)

ግብ ጠባቂ – ጀማል ጣሰው – መከላከያ

የብሄራዊ ቡድኑ ቁጥር አንድ በዋልያዎቹ ማልያ የሚያሳየው አቋም ቢያስተቸውም ባለፉት 4 ጨዋታዎች በጦሩ ቤት እያሳየ የሚገኘው አቋም ግን በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ጀማል የሚመራው የመከላከያ ግብ በዚህ ወር የተቆጠረበት ግብ 1 ብቻ መሆኑ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ የመከላከያ የተከላካይ ክፍል ጠንካራ ቢሆንም ለማጥቃት ከጀርባቸው ጥለውት የሚሄዱትን ክፍተት በመድፈን በኩል እንዲሁም ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማዳኑ ረገድ ጥሩ ወር አሳልፏል፡፡ የዳሽን ቢራው ደረጄ አለሙ እና የመብራት ኃይሉ ገመቹ በቀለ በዚህ ወር መልካም አቋም ካሳዩ ግብ ጠባቂዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ተከላካዮች – አወት ገ/ሚካኤል – መብራት ኃይል

አወት በዚህ ወር ብቻ ሳይሆን የውድደር ዘመኑ ከተጀመረ ጀምሮ ወጥ አቋም እያሳየ ሲሆን በተለይም በመከላከል ላይ ያለው አቋም ከፍተኛ ነው፡፡ የሃይል አጨዋወቱ ፣ ሸርታቴውና አንድ ለአንድ በሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ያለው የበላይነት ታላቅ ወንድሙ ዮናስ ገ/ሚከኤልን ያስታውሰናል፡፡ ባለፈው ወር በምርጥ 11 የተካተተው አብዱልከሪም መሃመድ እና ሽመልስ ተገኝ በቀኝ መስመር በወሩ ድንቅ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በረከት ተሰማ – መብራት ኃይል

በረከት ተሰማ ከዘንድሮው የመብራት ኃይል ጥንካሬ ጀርባ የሚጠቀስ ተከላካይ ነው፡፡ በእርጋታ የተከላካይ ክፍሉን የመምራት ብቃቱን በዚህ ወር አሳይቶናል፡፡ ከሁሉም በላይ በቀዮቸ ቤት ዘንድሮ ካለ ቋሚ አጣማሪ የተጫወተው በረከት ከሁሉም አጣማሪዎች (ሲሳይ ፣ አዎይኒ ሚካኤል እና አልሳዲቅ አልማሂ) ጋር ያለው መናበብ ጥሩ ነው፡፡

ኤፍሬም ወንድወሰን – ኢትዮጵያ ቡና

ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ኤፍሬም በውዝግብ ከሜዳ የራቀው ቶክ ጄምስን ቦታ በሚገባ ሸፍኗል፡፡ ቁመተ ረጅሙ ኤፍሬም የቡናን የአየር ላይ ኳስ ችግር በመጠኑ ከመቅረፉ ባሻገር ከቶክ በተሸለ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ተሳትፎ መልካም የሚባል ነው፡፡ የመከላከያው ተስፋዬ በቀለ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላዲን በርጊቾ በቦታው ጥሩ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ዘካርያስ ቱጂ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወጣቱ የግራ መስመር ተከላካይ በከፍተኛ ገንዘብ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው መሃሪ መናን አስረስቷል፡፡ ከመሃሪ እና አለማየሁ ሙለታ ቀድሞ የአሰልጣኝ ኔይደር ዶ ሳንቶሰን እምነት ያገኘ ሲሆን ከሲቲ ካፑ ጀምሮ እስካሁን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ዘልቋል፡፡ በዚህ ወር በተለይም ከሙገር ሲሚንቶ ጋር ምርጥ አቋሙን አሳይቷል፡፡

አማካዮች – ጋቶች ፓኖም – ኢትዮጵያ ቡና

የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ በዚህ ወር ከኢትዮጵያ ቡና ማንሰራራት ጋር አብሮ የሚጠቀስ ተጫዋች ነው፡፡ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢትን ሲረታ ድንቅ አቋም ያሳየ ሲሆን የማጥቃት ባህርይ ባላቸው አማካዮች የተሞላው ኢትዮጵያ ቡናን ሚዛን በመጠበቁ ረገድም የሚታይ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ዳዊት እና መስኡድ ባልተሰለፉባቸው ጨዋታዎች ቡናን በአምበልነት መርቷል፡፡ የአርባምንጭ ከነማው ሙሉአለም መስፍን እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ናትናኤል ዘለቀ ሌሎች በቦታው ድንቅ አቋማቸውን በዚህ ወር ካሳዩን መሃል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የተሻ ግዛው – ዳሽን ቢራ

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከታዩ በክህሎት የበለፀጉ ተጫዋቾች መካከል የተሻ አንዱ ቢሆንም ኒያላን ከለቀቀ ወዲህ በተዛወረባቸው ክለቦች ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት ቆይቶ ዘንድሮ በዳሽን ቢራ ማንነቱን ማሳየት ጀምሯል፡፡ የመስመር አማካዩ በማጥቃት አጨዋወቱ ደካማ በሆነው ዳሽን ቢራ ጎልቶ መውጣት ችሏል፡፡ በራሱ ጥረት ግቦች ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ከመስመር የሚያሻግራቸው አደጋ ፈጣሪ ኳሶች በዚህ ወር ጎልተው ወጥተዋል፡፡

አስቻለው ግርማ – ኢትዮጵያ ቡና

አመቱን በጉዳት የጀመረው አስቻለው ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት መሳርያ ሆኗል፡፡ በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የማሸነፍያዋን ግብ ሲያስቆጥር አዳማ እና ደደቢት ላይም ድንቅ አቋሙን አሳይቷል፡፡ ፍጥነቱ ፣ የሚያሻግራቸው ኳሶች እና የሚያስቆጥራቸው ግቦች ለወሩ ኮከብነት የሚያሳጩ ናቸው፡፡

አጥቂዎች – ብሩክ አየለ – ሲዳማ ቡና

የሲዳማ ቡናው ኮከብ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሀዋሳ ከነማ እና ደደቢትን ሲረቱ ግሩም አቋም አሳይቷል፡፡ በዚህ ወር 2 ግቦች ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን በተለይም ደደቢት ላይ ያስቆጠራት ግብ የግል ክህሎቱን ያሳየባት ነች፡፡

አላዛር ፋሲካ – ወላይታ ድቻ

የወላይታ ድቻው አጥቂ ካለጥርጥር የዘንድሮው ክስተት ነው፡፡ ያለፉትን 2 የውድድር ዘመናት በድቻ ቢቆይም እንደዚህ አመት ምርጥ አቋሙን ያሳየበት ጊዜ የለም፡፡ ድቻ ሀዋሳ ከነማ ፣ ወልድያ ፣ አዳማ እና መከላከያን በተከታታይ በረታበት ጨዋታ ድንቅ አቋሙን ሲያሳይ 2 ግቦችንም ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከባዬ ገዛኸኝ ጋር የፈጠሩት ጥምረትም በሊጉ ከሚገኘ ምርጥ ጥምረቶች አንዱ ሆኗል፡፡

ቢንያም አሰፋ – ኢትዮጵያ ቡና

አምና በአጥቂ ክፍሉ ደካማነት ሲተች የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በቢንያም አሰፋ በትክክል መጥቀም ጀምሯል፡፡ ቢንያም ከሲቲ ካፑ ጀምሮ ግቦች በቋሚነት እያስቆጠረ ሲሆን ከአማካዮቹ ጋርም ድንቅ ጥምረትን ፈጥሯል፡፡ የድቻው ባዬ ገዛኸኝ ፣ የመብራት ኃይሉ ዮርዳኖስ አባይ እና የመከላከያው መሃመድ ናስር ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባቸው አጥቂዎች ናቸው፡፡

የህዳር / ታህሳስ ወር ኮከብ አሰልጣኝ – መሳይ ተፈሪ

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በድጋሚ የሊጉ የመወያያ ርእስ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ አምና ተከታታይ ጨዋታዎችን አቻ በመውጣት ብዙዎችን ያስገረመው የመሳይ ተፈሪ ቡድን በዚህ ወር ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በድል በመወጣት ጠንካራነቱን አሳይቷል፡፡ ለወትሮው በተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ ታግዞ በአሸናፊነት የሚወጣው ቡድን ዘንድሮ ግቦች በማስቆጠር የሚያሸንፍ ቡድን ሆኗል፡፡ ለዚህ ለውጥም አሰልጣኝ መሳይ የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ ክብር ይገባዋል፡፡

የህዳር / ታህሳስ ወር ኮከብ ተጫዋች – ቢንያም አሰፋ

ባለፈው ወር ሳሚ ሳኑሚ ድንቅ እንደነበረው ሁሉ ቢንያም በዚህ ወር ባስቆጠራቸው ግቦች ከሌሎች ጎልቶ መውጣት ችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከ4 ጨዋታዎች 10 ነጥብ እንዲያገኝ የቢንያም 4 ግቦች የጎላ ሚና ነበራቸው፡፡ የጨዋታ ዘመኑ ያበቃለት መስሎ የነበረው ቢንያም አሁን በሊገ ከሚገኙ ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *