ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነገሌ አርሲ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነገሌ አርሲ ነጥብ ተጋርተዋል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነገሌ አርሲ ያገናኘው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ5 ኛው ሳምንት የምድብ ሁለት የመጀመርያ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዋና ዳኛ አብርሃም ኮየራ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ኤሌክትሪኮች መጠነኛ የሚባል ብልጫ የወሰዱበት ነበር። 14ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ሸዋለም በጭንቅላቱ ወደኋላ በመግጨት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀሰን ሁሴን በድንቅ ሁኔታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ በጥሩ ቅልጥፍና የመለሰው ኳስም በአጋማሹ የታየ የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነው።

ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ይኑር እንጂ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በተደጋጋሚ በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ነጌሌ አርሲዎች ነበሩ። ሰገኖቹ አለኝታ ማርቆስ 67ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረገውና በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ከወጣበት ሙከራ በኋላም ጨዋታው 86ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በመልሶ ማጥቃት የወሰዱትን ኳስ ሀቢብ ከማል በደካማ እግሩ ከቀኝ መስመር የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ ያንኑ ኳስ ያገኘው ኢብሳ በፍቃዱ ተገልብጦ ያደረገውን ጥሩ ሙከራ ግብ ጠባቂው አሸብር ተስፋዬ በቀላሉ ይዞበታል። በሙከራዎች ያልታጀበው የምድብ ሁለት የመጀመርያ ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።