ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ

ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ5ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ላይ ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል።

ምድረገነት ሽረ ከ ሲዳማ ቡና

ጥሩ ፉክክር እና በርከት ያሉ ሙከራዎች በታዩበት የመጀመርያው አጋማሽ ሽረ ምድረገነት በመልሶ ማጥቃት ሲዳማ ቡና በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር። ሲዳማ ቡናዎች ፌደሪክ ኑሲ እንዲሁም ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ሞክሯት ግብ ጠባቂው በአስደናቂ ብቃት በመለሳት ኳስ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ቀድመው ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ሽረ ምድረገነቶች ነበሩ። በ11ኛው ደቂቃ አቤል ማሙሽ ከሽመክት ጉግሳ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ሽረዎችን መሪ ማድረግ  ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሲዳማ ቡናዎች ብለሥ ናጎ በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች፤ ሽረ ምድረ ገነቶች ደግሞ በአቤል ማሙሽ አማካኝነት ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም አጋማሹ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር። ተመስገን በጅሮንድ ከመስመር አሻግሯት ብለሥ ናጎ ከሞከራት በኋላ ግብ ጠባቂውን አልፋ ወደ ግብነት ከመቀየሯ በፊት ክፍሎም ገብረሕይወት ከመስመሩ የመለሳት ወርቃማ ዕድልም ሲዳማ ቡናን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። በ62′ ደቂቃም ሲዳማዎች የፈጠሩት ጫና ፍሬ አፍርቶ አስቻለው ሙሴ ከመስመር አሻግሯት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በግንባር ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ከግቧ በኋላ በ67′ ደቂቃ የሽረ ምድረገነቱ ክፍሎም ገብረሕይወት በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 8′ ደቂቃዎች ሲቀሩትም መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር አሻግሯት ብርሃኑ በቀለ በግንባር ያስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናዎችን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቧ በኋላ መስፍን ታፈሰ በሁለት አጋጣሚዎች ካደረጋቸው ሙከራዎች በኋላም ጨዋታው በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቀዝቃዛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበትና በሙከራዎች ባልታጀበው የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ድሬዳዋ ከተማዎች ብልጫ ያሳዩበት ሲሆን በብርቱካናማዎቹ በኩል አስራት ቱንጆ ከሳጥን ውጭ ያደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ በወልዋሎ በኩል ደግሞ ሰመረ ሀፍታይ  ከመስመር አሻግሯት ኮንኮኒ ሐፊዝ ያልተጠቀመባት ኳስ ይጠቀሳሉ። በ37ኛው ደቂቃ ግን አብዱልሰላም የሱፍ ከመዓዝን አሻምቷት ያሬድ ታደሰ በግንባር ያስቆጠራት ግብ ድሬዳዋ ከተማዎችን መሪ ማድረግ ችላለች።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ በእንቅስቃሴ ረገድ መጠነኛ መሻሻል የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የጀመሩት ሲሆን ነፃነት ገብረመድኅን ከመዓዝን ምት ተሻምታ ተከላካዮች በአግባቡ ያላራቋት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እንዲሁም ኮንኮኒ ሐፊዝ በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ አብርዶ ሞክሯት አሕመድ ረሺድ በጥሩ መንገድ ተደርቦ ያወጣት ሙከራ በወልዋሎ በኩል ይጠቀሳሉ። በ68′ ደቂቃ ላይ ግን አብዱሰላም የሱፍ በግሩም መንገድ ከመሀል ሜዳ እየገፋ ወደ ሳጥን ይዟት ገብቶ በጥሩ መንገድ ከፍ አድርጎ ከመረቡ ጋር ባዋሀዳት ኳስ ብርቱካናማዎቹ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 8 ደቂቃዎች ሲቀሩትም ወልዋሎዎች ብሩክ እንዳለ አሻግሯት ዳዊት ገብሩ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ባስቆጠራት ግብ ወደ ጨዋታው ቢመለሱም በቀሪ ደቂቃዎች ግብ ባለማስቆጠራቸው ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።