ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ5ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ5ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ከመቋረጡ በፊት የሚደረጉ አራት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

አርባምንጭ ከተማን በገጠሙበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ግብ እና ድል ያገኙት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ የድል መንገዳቸውን ማስቀጠል ዋነኛ ዓላማቸው ነው። አዳማዎች በ3ኛ ሳምንት ላይ አዞዎቹን ድል ማድረግ ቢችሉም ለ49′ ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደደው ተጋጣሚያቸው ላይ የወሰዱት ብልጫ ግን ደረት የሚያስነፋ አልነበረም። በዛሬው ጨዋታም በማጥቃት አጨዋወታቸው ጥራት ላይ በርከት ያሉ ማሻሻያዎች ማድረግ ግድ ይላቸዋል።

በመጨረሻው ሳምንት የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን የቀመሱትና በአራት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከገጠማቸው ሽንፈት አገግመው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሽንፈት በገጠማቸው መርሐግብር በቀደሙት ጨዋታዎች ከነበራቸው የማጥቃት ጥንካሬ በብዙ ረገድ ተዳክመው የታዩት ቡናማዎቹ በሊጉ ምንም ግብ ያልተቆጠረበትን የአዳማ ከተማ የኃላ ክፍል ሊፈትን በሚችል የፊት መስመር ጥንካሬ መቅረብ ግድ ይላቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 46 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 24 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 10 ጊዜ ድል ሲቀናው በ12 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 79 ፤ አዳማ 42 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ ያስመዘገቧቸው ድሎች ወደ ሦስት ያሳደጉት ሀዋሳ ከተማዎች አሁን ካሉበት 5ኛ ደረጃ ይበልጥ ወደ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በአፈፃፀም ረገድ ሲለካ በግሩም ብቃት ላይ የሚገኝ የፊት መስመር ያላቸው ሐይቆቹ እምብዛም የጠራ የግብ ዕድል ባልፈጠሩበት የመጨረሻው ጨዋታ ያስቆጠሩት የግብ መጠን የፊት መስመሩ አሁናዊ ብቃት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በዛሬ ጨዋታም ለባንክ ተከላካዮች ፈተና መሆናቸው የማይቀር ነው።

በመቻል ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው በመጨረሻው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ማሸነፍ የቻሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ነጥባቸውን አምስት በማድረስ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ድሬዳዋ ከተማን ባሸነፉበት መርሐ-ግብር በመጀመርያዎቹ ሦስት ሳምንታት ካሳዩት በብዙ ረገድ የተሻሻለ እንቅስቃሴ የነበራቸው ሀምራዊ ለባሾቹ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማጎልበት እንዲሁም ለውጤታማው የሀዋሳ የፊት መስመር ማቆም የሚችል የመከላከል ውቅር ማበጀት ይኖርባቸዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ እና ቢንያም በላይ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ ከዚህ በተጨማሪም በመጨረሻው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው በረከት ሳሙኤል ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በመጨረሻው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፈው ተከላካዩ ካሌብ አማንክዋህ ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ነገር በአሰልጣኙ የሚወሰን ይሆናል።

በሊጉ 39 ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በ13 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ15 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በ11 ጨዋታዎች ድል ማድረግ ችለዋል። በጨዋታዎቹ ንግድ ባንኮች 43፤ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ 39 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ሸገር ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ በታሪካቸው የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ድል ያገኙት ሸገር ከተማዎች ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸው አስመዝግበው ነጥባቸውን ሰባት ለማድረስ ሀድያ ሆሳዕናን ይገጥማሉ። በሁሉም ረገድ ብልጫ በወሰዱበት የመጨረሻው ጨዋታ ዘነበ ከድር በተሰለፈበት የግራ መስመር በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር የቻሉት ሸገሮች በጥቅሉ ሲታይ የሚያስወድስ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ዕድሎችን የመጠቀም ጉልህ ድክመታቸው ግን መታረም የሚገባው ነው።

ከአራት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ሰብስበው 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ሸገር ከተማን ይገጥማሉ። ነብሮቹ በመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ቢያስተናግዱም ያሳዩት እንቅስቃሴ ግን ለትችት የሚዳርግ አልነበረም። የቡድኑ የፊት መስመር ጥምረትም ከጨዋታ ጨዋታ በጎ ለውጦች ማሳየት ቢችልም በግብ ፊት ያለበትን የአፈፃፀም ድክመት ማረብ ግድ ይለዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ነገ በፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጨዋታቸውን  ያደርጋሉ።

መቻል ከ ፋሲል ከነማ

በተመሳሳይ አስር ነጥብ የሰበሰቡ፤ በአራት ሳምንታት ጉዞ ሽንፈት ያልቀመሱና በግብ ክፍያ ተበላልጠው የሊጉን አናት ለመቆናጠጥ የሚፋለሙትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ እጅግ ተጠባቂ ነው። በመርሐግብሩም በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦችን እያስቆጠረ የዘለቀው አስፈሪው የጦሩ የፊት መስመር እና ካከወናቸው አራት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የዐፄዎቹ የመከላከል ክፍል የሚያደርጉት ፍልሚያ እጅግ ተጠባቂ ነው። ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ የሚወጣ ቡድን ቢያንስ ሊጉ በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ለአስር ቀናት ተቋርጦ ዳግም እስኪመለስ ድረስ በሰንጠረዡ አናት መቀመጥ ይችላል።

በፋሲል ከነማ በኩል ዮሐንስ ደርሶ በጉዳት እንዲሁም ብሩክ አማኑኤል በቅጣት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ቃልኪዳን ዘላለም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በመቻል በኩል መሐመድ አበራ እና ፈቱዲን ጀማል በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ 7 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻል 4 ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው። ፋሲል 21 ሲያስቆጥር መቻል 12 ግቦች  አስቆጥሯል።