በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ተቋርጦ የነበረው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ሲዳማ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ
ካከናወኗቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ድሎች እና አንድ ሽንፈት በማስተናገድ በአስራ ሁለት ነጥቦች በሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ተከታታይ ሦስተኛ ድላቸውን አሳክተው መሪነታቸውን ለማጠናከር ወደ ሜዳ ይገባሉ። ዘጠኝ ግቦች በማስቆጠር ከሊጉ ቀዳሚ የሆነ የአጥቂ ክፍል ያላቸው ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፤ በዛሬው ዕለትም በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ቀዳሚ ለሆነው የመቐለ 70 እንደርታ የተከላካይ ክፍል ፈተና መሆናቸው አይቀሬ ነው።
በሊጉ የመጀመርያ ድላቸውን ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡት መቐለ 70 እንደርታዎች በሁለት ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ምዓም አናብስት ስድስት ግቦች በማስቆጠር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጣምራ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለቦች ዝርዝር 3ኛ ደረጃ መቀመጥ ቢችሉም በአማካይ በጨዋታ ሁለት ግቦች በድምሩ አስር ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ግን ዋነኛ ድክመታቸው ነው። በዛሬው ዕለትም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን እንደመግጠማቸው በብዙ ረገድ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል።
በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል ፍሬዘር ካሳ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም እንዲሁም የጊትጋት ኩት መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። በሲዳማ ቡና በኩል አበባየሁ ሀጂሶ አሁንም በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም ደግፌ ዓለሙ ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
ቡድኖቹ እስካሁን ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች መቐለ 70 እንደርታዎች ሦስት ጊዜ ድል ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል ፤ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው ከተቆጠሩት 12 ጎሎች መቐለ ሰባት ሲያስቆጥር ሲዳማ አምስቱን አስቆጥሯል።
ነገሌ አርሲ ከ አዳማ ከተማ
ሦስት አቻ እንዲሁም ሁለት ሽንፈቶች አስመዝግበው
በሦስት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነገሌ አርሲዎች በታሪካቸው የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ድል ለማግኘት አዳማ ከተማን ይገጥማሉ። ነገሌ አርሲዎች በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ቀዳሚ ስራቸው እንደሚሆን እሙን ነው። ቡድኑ ምንም እንኳን ጠንካራ ቡድኖች በገጠመባቸው የተጠቀሱ ጨዋታዎች ላይ በሁለቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ አወንታዊ ነገር ቢያስመለክትም ጠንካራ የኋላ ክፍል ያለው ቡድን በሚገጥምበት የዛሬው ጨዋታ የማጥቃት አጨዋወቱን ማሻሻል ግድ ይለዋል።
ከተከታታት ሦስት የአቻ ውጤቶች በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውን ዘጠኝ በማድረስ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ወደ ሊጉ አናት ለመጠጋት ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። አዳማ ከተማ በሊጉ መረቡን ያላስደፈረው ብቸኛ ቡድን ሲሆን የመከላከል አደረጃጀቱም ዋነኛው ጥንካሬው ነው። ሆኖም እስካሁን ድረስ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው የማጥቃት አጨዋወት ማስተካከል አሰልጣኝ ስዩም ከበደን የሚጠብቃቸው ስራ ነው።
በነገሌ አርሲ በኩል አብዱልባሲጥ ከማል ፣ ኢብሳ በፍቃዱ እና በረከት ወልዴ በጉዳት ተስፋዬ በቀለ ደግሞ በኢትዮጵያ ዋንጫ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት በቅጣት በዛሬው ጨዋታ አይሳተፉም። በአዳማ ከተማ በኩል ያለው የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ በታሪካቸው የመጀመርያው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያከናውናሉ።


