በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ምድረገነት ሽረ
ሁለት ከአቻ ውጤት የተመለሱ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ 07፡00 ሲል ይደረጋል።
ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ዝግ ያለ አጀማመር አድርገው በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ወደ ጨዋታው ቀስ በቀስ ተመልሰው ጎል ሳያስተናግዱ ነጥብ የተጋሩት ብርቱካናማዎቹ በየጨዋታው የሚታይባቸው የወጥነት ችግር ማለትም በማራኪ አቀራረብ ቡድኑ ድል ቢያደርግም በቀጣዩ ጨዋታ ከሚጠብቃቸው ተጠባቂነት አንጻር እየተቀዛቀዙ መምጣታቸው ተከታታይ ድሎችን እንዳይቀዳጁ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
ከመቻል ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጠንካራ ሆነው የቀረቡት ምድረገነት ሽረዎች ጨዋታውን መምራት ችለው ተከታታይ ጎሎችን ቢያስተናግዱም የኋላ የኋላ የአቻነት ግብ አስቆጥረው አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። ከእንቅስቃሴ አንጻር ጠንካራ የሚባለው ቡድኑ በራስ መተማመኑን ከፍ አድርጎ ድል ማሳካት ይኖርበታል።

በድሬዳዋ በኩል ሙኸዲን ሙሳ እና አብዱልሰላም የሱፍ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን በምድረገነት ሽረ በኩል ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
በ2011 ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ ከተሰረዘው እና የአቻ ውጤት ከተመዘገበበት የ2012 ጨዋታ ውጭ 4 ጊዜ ተገናኝተው በሦስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው ያለፈውን ዓመት የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ድሬዳዋ አሸንፏል። በግንኙነቱ ድሬዳዋ ከተማ ስድስት ምድረገነት ሽረ ደግሞ አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበው የተመለሱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ የምድብ አንድ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነው።
ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፈው በሦስቱ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ምዓም አናብስት ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች መልስ ወደ ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መመለሳቸው እንደ መልካም ጎኑ የሚነሳላቸው ነው። በአምስት ጨዋታዎች 10 ግቦችን አስተናግዶ የነበረው ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በቀይ ካርድ ተጫዋች ቢወጣበትም የሲዳማ ቡናን ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ መግታቱ ለዛሬው ጨዋታ በተለይም የኋላ መስመሩ ላይ የሚፈጥረው መነቃቃት ይጠበቃል።
ከፋሲል ከነማ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከመመራት ተነስተው ነጥብ መጋራት የቻሉት ንግድ ባንኮች በዘንድሮው የውድድር ዓመት የሚነሳላቸው ጠንካራ ጎን ይህ ነው። ቡድኑ በየጨዋታው በተጋጣሚ ቡድን የሚፈጠሩበትን በርካታ የግብ ዕድሎች ለመግታት የመከላከል ሽግግሩ ላይ በቶሎ ለውጥን ማምጣት አለበት።
መቐለ 70 እንደርታዎች ፍሬዘር ካሳ እና ዘርኢሰናይ ብርሃነን በቅጣት ጊትጋት ኮች፣ ዮሐንስ ዓፈራ እና ሐድሽ በርኸ ደግሞ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አያሰልፉም። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ዓመት ካደረጓቸው ሁለት የመጀመሪያ እርስ በእርስ ግንኙነቶች የመጀመሪያው ጨዋታ 0ለ0 ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በንግድ ባንክ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ አርባምንጭ ከተማ
ነብሮቹ እና አዞዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታ ነው።
ፈረሰኞቹን 1ለ0 አሸንፈው ከናፈቃቸው ድል ጋር የታረቁት ሀዲያዎች የዛሬውን ጨዋታ በመጠነኛ እፎይታ ውስጥ ሆነው ያደርጋሉ። ቡድኑ ባለፉት ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠሩም መጀመሪያ ሦስት ሳምንታት ላይ ከጎል ጋር ተለያይቶ ካሳለፈበት ጊዜ አንጻር ተሻሽሎ የቀረበበት ነው። ሆኖም ቡድኑ የዛሬው ጨዋታ ላይ ድል የሚያስመዘግብ ከሆነ ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ የሚፈጥርለት በራስ መተማመን ከፍ ያለ ነው።

እጅግ ደካማ አጀማመር እያደረጉ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ምንም ድል ካላሳኩ ሦስት ቡድኖች መካከል አንዱ ነው። ባለፉት ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑ ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ማጣቱ ለአሰልጣኝ በረከት ደሙ እጅግ ትልቅ የቤት ሥራ የሚሰጥ ነው (ይህ ችግር ባለፈው የውድድር ዓመትም በተደጋጋሚ ይስተዋል እንደነበር ልብ ይሏል)። አዞዎቹ የሚታወቁበትን ጠንካራ መከላከል አደረጃጀት አጥተው በስድስት ጨዋታ 7 ጎሎችን ማስተናገዳቸውም ሌላው በትልቁ የሚነሳ ጉዳይ ነው።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሄኖክ አርፊጮ እና ጄይላን ከማል ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው አይኖሩም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል በርናንድ ኦቼንግ እና አንዱዓለም አስናቀ አሁንም በጉዳት የዛሬው ጨዋታ ሲያመልጣቸው አካሉ አቲሞ ቡድኑ ከሸገር ከተማ ጋር ጨዋታ ሲያደርግ በሁለት ቢጫ ካርድ በመውጣቱ በቅጣት ጨዋታው ያመልጠዋል።
ቡድኖቹ በሊጉ ከተገናኙባቸው ስምንት ጨዋታዎች አምስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ሁለት ሀዲያ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል አድርገዋል። በጨዋታዎቹ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 11 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።

