ሪፖርት| ሀድያ ሆሳዕና እና አርባ ምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ሀድያ ሆሳዕና እና አርባ ምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

የሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተቆጠሩ የግንባር ግቦች ነብሮቹ እና አዞዎቹ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ባስመለከተን ጨዋታ 12ኛው ደቂቃ ላይ በአርባ ምንጩ ተጫዋች መሪሁን መስቀለ ከርቀት የመታው እና ግብጠባቂው ኦውሱ እንድሪውስ እንደምንም ብሎ ወደ ውጭ ያወጣው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ሁኖ የተመዘገበ ሲሆን ያንኑ የወጣውን እና ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ታምራት እያሱ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። 

ሌላ ሁለተኛ ግብ ለማስቅጠር ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዞዎቹ 30ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት ኤያሱ ተቀልብሶ ያቀበለውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ወደ ግብ ሞክሮ በግብ ጠባቂው የተመለሰ ሲሆን ያንኑ የተመለሰውን ኳስ ታምራት እያሱ በግንባሩ ጉጭቶ ቢሞክረውም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰ ሲሆን በድጋሚ በእግሩ የመታው ኳስ ለሁለተኛ ጊዜ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ለአዞዎቹ እጅግ አስቆጪ ለ ሀድያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ዕድለኛ የነበሩበት አጋጣሚ ነበር::

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ሀድያ ሆሳዕናዎች ራሳቸውን በማሻሻል በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን 60ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ በሚገርም ቅልጥፍና ሶስት የአርባምንጭ ተከላካዮችን አልፎ የሞከረው ኳስ ዒላማውን መጠበቅ ተስኖት ለጥቂት በግቡ ቋሚ ታኮ ወጥቷል። አሁንም ጫናዎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ነብሮቹ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ኢዮብ አለማየሁ በግንባሩ ገጭቶ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በሁለቱም ቡድኖች በተቆጠሩ የግንባር ግቦች 1-1 በሆነ አቺ ውጤት ተጠናቋል።