የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | የሦስተኛ ዙር የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | የሦስተኛ ዙር የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የኢትዮጵያ ዋንጫ የሦስተኛ ዙር ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲካሄዱ የዕለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ደብረ ብርሃን ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና

ሁለቱ የከፍተኛ ሊግ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ 07፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።

በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ አዲስ ከተማ ክ/ከተማን በመለያ ምት (7ለ6) አሸንፈው ወደ ሦስተኛው ዙር የተሸጋገሩት ደብረ ብርሃኖች በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” አምስት ጨዋታዎችን አድርገው አምስት ነጥቦችን በመሰብሰብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ እየተወዳደረ ከሚገኘው ቤንች ማጂ ቡና ጋር በሚያደርጉት የነገ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታም በከፍተኛ ሊጉ ካላቸው ቀዝቃዛ አጀማመር አገግመው ድል ለማድረግ ብርቱ ፍልሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ጋሞ ጨንቻን አሸንፈው ወደ ሦስተኛው ዙር ያለፉት ቤንች ማጂ ቡናዎች በተከታታይ ዓመታት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ በሚደረገው ፉክክር ጠንካራ ፍልሚያ ከሚያደርጉ ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ። ባለፉት ዓመታት በሊጉ ተፎካካሪ ቡድን በመገንባት የሚታወቀውና በዘንድሮ የውድድር ዓመት
በምድብ “ሀ” ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች 7 ነጥቦች  ሰብስቦ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በነገው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ድል መቀዳጀት ለሁለቱም ውድድሮች የሚፈጥርለት መነሳሳት ትልቅ እንደ መሆኑ ጨዋታው በቀላሉ እንደማይመለከተው እሙን ነው።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ንብ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ  ስታድየም 7፡00 ላይ ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት ወደ 9፡30 የተሸጋሸገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በሁለተኛው ዙር በኮንኮኒ ሀፊዝ እና ፍሬው ሰለሞን ግቦች ወላይታ ድቻን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ለሦስተኛው ዙር የበቁት ወልዋሎዎች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተቀዳጇቸው ድሎች የፈጠረላቸው በራስ መተማመን ከፍ ያለ ነው። ቢጫዎቹ በማጥቃቱና በመከላከሉ ረገድ እንዲሁም አጠቃላይ የቡድን መንፈሳቸው ላይ አወንታዊ ለውጦች ታይተዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ የፊት መስመር በብዙ ረገድ ተሻሽሎ የቀረበ ሲሆን በነገው ዕለትም ይህንን በቡድኑ የታየው ሁለንተናዊ ለውጥ ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

የካ ክፍለ ከተማን በመለያ ምት (4ለ2) አሸንፎ ወደ ሦስተኛው ዙር የተሸጋገረው ንብ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ አጀማመር በማድረግ ላይ ከሚገኙ ክለቦች ይጠቀሳል። እንደ ባለፉት ዓመታት ዘንድሮም ተፎካካሪ ቡድን በመገንባት በምድብ ‘ሀ’ ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች 12 ነጥቦችን ሰብስቦ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ንብ በሊጉ ያለውን አወንታዊ ጅማሮ በኢትዮጵያ ዋንጫም ለማስቀጠል በጥሩ መነቃቃት ከሚገኘው ወልዋሎ በሚያደርገው የነገው ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅበታል።

ሲዳማ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

በሃያ ነጥቦች የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመምራት ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በሊጉ ያላቸውን ውጤታማነት በኢትዮጵያ ዋንጫም ለማስቀጠል አዞዎቹን ይገጥማሉ። በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ሦስተኛው ዙር የተቀላቀለው ቡድኑ በፕሪምየር ሊጉ ባደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ስድስት ድሎች፣ ሁለት የአቻ ውጤቶች እንዲሁም አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ ድንቅ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛል። በነገው ዕለትም ደካማ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማን እንደ መግጠሙ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም በቅርብ ጨዋታዎች የተስተዋሉበትን የአፈፃፀም ድክመቶች መቅረፍ ይኖርበታል።

በሲቢኢ ፕሪምየር ሊግ ድል ማድረግ ካልቻሉ ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካለው መጥፎ አጀማመር ተላቆ በኢትዮጵያ ዋንጫ ድል ማድረግን እያለመ ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባል። በሁለተኛው ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምት አሸንፎ ሦስተኛውን ዙር የተቀላቀለው ቡድኑ በፕሪምየር ሊጉ ባደረጋቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ማሳካት የቻለው ሁለቱን ብቻ ሲሆን የግብ ማስቆጠር ድክመትም ዋነኛው ችግሩ ነው።

በነገው ጨዋታ ድል አድርጎ ወደ ቀጣዩ ዙር ለመሻገርም በማጥቃቱም ይሁን በመከላከሉ በሊጉ ጠንካራ ጥምረት ካላቸው ክለቦች አንዱ ለሆነው ተጋጣሚው ሊመክት በሚችል አኳኋን መቅረብ ግድ ይለዋል። አዞዎቹ በተለይም የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታን ጨምሮ በመጨረሻዎቹ ሰባት መርሐግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።