(ዘለግ ያለ ፅሁፍ የማይሆንለት ሰው የመጨረሻውን አንቀፅ ብቻ በማንበብ ጭብጤን ማግኘት ይችላል)
ሳሙኤል ስለሺ
ባለፉት ሁለት እና ሦስት ቀናት ሲዘዋወሩ ከነበሩ ስፖርታዊ ፎቶዎች መካከል አንዱ ሰፊ ትኩረት እና የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሲያልፍ ሁለተኛው ብዙም ሳይወራለት እንዲሁ ተሸፋፍኖ ቀርቷል። ሁለቱም ፎቶዎች የአርባ ምንጭ ከነማን ባንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሚያሳዩ ሲሆን የመጀመሪያው ፎቶ የቡድን አባላቱ በአንድ የማነቃቂያ ስልጠና ላይ ከአሰልጣኛቸው ፊት ተቀምጠው እራሳቸውን ለጨዋታ ሲያዘጋጁ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በልምምድ ሜዳ ላይ እለታዊ ስልጠናቸውን እየወሰዱ የሚያሳይ ነው። ሁለቱም ስልጠና (ይሄ ቃል ብዙም ምቾት አይሰጠኝም፥ ብቻ ስለሚያግባባን ይሁን እንጂ) ናቸው፥ ሁለቱም ትምህርት ናቸው፥ ሁለቱም የተጨዋቾችን ብቃት ለማሳደግ እና ወደ አቋምነት ለመተግበር የሚደረጉ ርብርቦሽ ናቸው።
መነጋገሪያ ስለሆነው የመጀመሪያው ፎቶ /ስልጠና/ በበጎም ሆነ በክፉም ብዙ ነገር ማለት ቢቻልም የበለጠ ልቤን የነካው እና ያሳዘነኝ ፎቶ ግን ሁለተኛው ሆኖ ስላገኘሁት ስለእሱ አስተያየት ለመስጠት እና ለሶከር ኢትዮጵያ ቤተሰቦች ለማጋራት ወደድሁ።

ብዙዎች እግር ኳስ እንደ ሐይማኖት ነው ሲሉ ይደመጣሉ፤ «እግር ኳስ አለም አቀፍ ሀይማኖት ነው» የሚሉትም አልታጡም። ፔሌ «እግር ኳስ እንደ ሀይማኖቴ ነው፤ ኳሷን አመልካታለሁ እንደ ፈጣሪዬም አገልግላታለሁ» ያለውን ለዚህ እንደመነሻ መውሰድ ይቻላል። አርባምንጭን በተለያየ አጋጣሚ እንደጎበኘ ከከተማዋ ታዳጊዎች፥ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች እንዲሁም ማህበረሰብ ጋር በተለያዩ ጊዜያት አብሮ ለመስራት እንደቻለ ባለሙያ አርባምንጮች እና እግር ኳስ ያላቸውን የመንፈስ ጋብቻ ለመረዳት የፔሌ ምስክርነት አያስፈልገኝም። (ካልተሳሳትኩ እና ካልተቀየረ በስተቀር የከተማዋ ኦፊሴላዊ አርማ ላይ ኳስ እንዳለ በአንድ ወቅት ለማስተዋል ችዬ ነበር)።
ለብራዚሎች፥ አርባ ምንጮች እና ሌሎች እግር ኳስ ወዳድ ህዝቦች እግር ኳስ በዚህ ደረጃ ከመንፈስ ጋር የሚተሳሰር ጉልበት እና አቅም ያለው ስፖርት ነው። ስለሆነም እግር ኳስ የሚዘወተርባቸው ቦታቸው በዛው ልክ እግር ኳሱ የሚከበርበት እና የሚወደስበት ፅዱ እና ቅዱስ ቦታዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል። ከእነዚህ መሀከል የልምምድ ቦታዎች፥ ስቴዲየሞች፥ የተጨዋቾች ማረፊያ፥ መሰብሰቢያ አዳራሾች፥ የተጨዋቾች ሰርቪሶች ይሄንን ጤናማ መንፈስ ሊያፈልቁ ብሎም ሊያቆዩ የሚችሉ መሆን አለባቸው። በተለይም በአንድ ሀገር ፕሪሚየር ሊግ ላይ ለደረሰ ክለብ፥ አመታዊው በጀቱ በ100 ሚሊዮኖች ለሆነ ክለብ ተጨዋቾቹ በጤናማ እግር ኳሳዊ ድባብ ውስጥ የመሰልጠን፥ የማደግ እና የመጎልበት እድል ሊመቻችላቸው ይገባል።
አንድ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተወዳዳሪ ክለብ የእለት ተእለት ልምምድ የሚሰራበት ሜዳ ይህንን ይመስላል ቢባል «ውሸታም» ያሰኛል። ምንም እንኳን በፎቶው ላይ የሚታየው የአርባምንጭ ከነማ ክለብ ቢሆንም ሁሉም ክለቦች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በእንደዚህ አይነት የልምምድ ሜዳ ላይ ቢያንስ ላለፉት አምስት አመታት ይሰሩ እንደነበር ለማስተዋል ችያለሁ። በቅርቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቲክቶክ ገፁ ላይ የለቀቀው ቪዲዮም ይሄንኑ ያመለክታል፥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን እራሱ በገነባው አካዳሚ ደረጃውን የጠበቀ የልምምድ ሜዳዎች ቢኖሩትም ለውድድር ሲወጣ ግን በመሰል ሜዳዎች ላይ ለመስራት ይገደዳል። ስለሆነም ይህ ፅሁፍ በአርባ ምንጭ ተንደረደረ እንጂ ሁሉንም ክለቦች ይመለከታል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስልጠና አሁን አሁን ስላቅ እና ፌዝ እየሆነ መጥቷል። ግብ ጠባቂዎች ድንጋይ ለቅመው ልምምድ የሚሰሩባቸው ሜዳዎች፥ አንዳንዴም ከሜዳው መበላሸት የተነሳ ላለመወርወር ሲሉ «ቮሊቮሊ» ብቻ ተጫውተው ልምምዳቸውን የሚጨርሱባቸው ሜዳዎች፥ እንደ ፒዛ ለአራት ክለቦች የተሸነሸኑ የልምምድ ሜዳዎች፥ ግማሽ አፈር ግማሽ ሳር አለፍ ሲልም ቀይ አሸዋማ ሜዳዎች የሀገሪቱ ቁንጮ ሊግ፥ የሀገሪቱ ቁንጮ ክለቦች፥ የሀገሪቱ ቁንጮ ተጨዋቾች የሚሰለጥኑባቸው «ቤተ መቅደሶች» ናቸው ቢባል ማን ያምናል? በፎቶው ላይ እንዲህ ባለ አቧራማ ሜዳ ላይ አቀርቅሮ ኮን የሚደረድረው አሰልጣኝ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ታሪክ እና አሻራ ካላቸው ተጨዋቾች መሀከል አንዱ የሆነው አበባው ቡጣቆ መሆኑ ደግሞ የፎቶውን ትርጉም አጉልቶ ያሳያል። በዛ ደረጃ የተጫወተ ተጨዋች በታዳጊነቱ በሚያውቃቸው ሜዳዎች ላይ በዚህ ደረጃ ላይ እንኳን ሆኖ ለማሰልጠን መብቃቱ ምንያህል እግር ኳሱ እዛው ሰፈሩ ውስጥ እንደቆመ ማስረጃ ነው። አበባው በታዳጊነቱ የቦረቀበት ሜዳ በአርባ ምንጭ በኩል አድርጎ እስከ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቶ፥ ብሄራዊ ቡድን ገብቶ፥ ጫማ ሰቅሎ፥ አሰልጣኝነት ፈቃድ ወስዶ ሲመጣ ያጋጠመው የልምምድ ሜዳ ያ በ1980ዎቹ የሚያውቀው የሰፈሩ ሜዳ ሆኖ ማግኘቱ ምን ያህል 30 እና 40 አመታትን እንዳባከንን ማሳያ ነው።
በእኔ አረዳድ የእግር ኳስ አስኳል «የእግር ኳስ ታለንት» ነው፤ ይህ ደግሞ የሚገኘው እግር ኳስ ተጫዋች ውስጥ ብቻ ነው። ተጫዋች በሌለበት ሁኔታ እግር ኳስ ጨዋታን ማሰብ አይቻልም። እግር ኳስ ያለ አሰልጣኝ ሊከናወን ይችላል ብዬ ብከራከር ሳላሳምን አልቀርም፥ ያለደጋፊም ሆነ ዳኛ ከመደረግም የሚያግደው ነገር አይኖርም፥ አመራርም ሆነ ምሁር ወይም ሚዲያ የተጫዋቹ ተከታይ ነው ብዬ ነው የምረዳው። ጥበብ እና ችሎታ ያለው ተጫዋች የእግር ኳስ አስኳል ነው። ይህ አስኳል የሚለመልመው ደግሞ የስልጠና ቦታዎች ላይ ብቻ ነው። ስልጠና በሜዳ፥ ስልጠና በክፍል ውስጥ፥ ስልጠና በጂምናዚየም፥ ስልጠና አንድ ለአንድ፥ ስልጠና በዲፓርትመንት፥ ስልጠና በቡድን ሊደረግ ይችላል። አሁን አሁን ከስልጠና ይልቅ በስብሰባ የተጨዋቾችን አቅም እና ችሎታ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት የበለጠ ሚዛን እየደፋ የመጣ ይመስል አንድ ክለብ ውጤት ሲያጣ የቦርድ አመራሮች አሰልጣኞችን ለብቻ፥ ሲኒየር ተጫዋቾችን ለብቻ፥ አንዳንዴ በጋራ ሰብስበው ያወያያሉ… ይወያያሉ። ጥሩ ነው፥ መነጋገር በራሱ አይከፋም። ይሄ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተቀዳ ውስጣዊ ግምገማ ግን ስልጠናን አይተካም፥ ልምምድን አይወክልም። ስልጠና እና ልምምድ እንዲህ ባለ ሜዳ እየተከናወነ የአዳራሽ ስብሰባ የሚፈይደው ነገር አይኖርም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጨዋቾች በመቶ ሺህ ዎች ደሞዝ የሚከፈላቸው፥ ባሸነፉ ቁጥር ማበረታቻ የሚሰጣቸው፥ በቀን ሶስት ወይም አራቴ ቀለብ የሚሰፈርላቸው፥ ማረፊያ ቦታ ተመቻችቶላቸው፥ እንዳይጉላሉ አልጋ የሚያነጥፍ፥ ምግብ የሚያበስል ተቀጥሮላቸው ሙሉ ትኩረታቸው አቋማቸው ላይ ብቻ እንዲሆን ተሰባስበው የሚገኙ «የተመረጡ፥ የተለዩ፥ የተሻሉ» ኢትዮጵያውያን ናቸው። ለችሎታቸው መዳበር ሶስት ወይም አራት አሰልጣኞች በዙሪያቸው ያሉ፥ አንዳንዴም የምግብ ባለሙያ የሚደግፋቸው፥ በቪዲዮ አናሊስት የሚታገዙ፥ አልፎ አልፎም በ«አነቃቂዎች» ድጋፍ የሚደረግላቸው የሀገሪቷ የእግር ኳስ ጣራ ናቸው።
ይህ ሁሉ ሽር ጉድ ግን ደረጃውን በጠበቀ ስልጠና ካልተመራ የውሸት ነው፤ የከንቱ ከንቱ…ጉንጭ አልፊ እና ሐሳዊ (ሐሰተኛ) ነው። ለአንድ እግር ኳስ ተጨዋች ወይም ክለብ «ስልጠና» እጅግ ወሳኙ የስራ ምዕራፍ ሲሆን አሰልጣኞች የእውቀታቸውን የመጨረሻውን ጫፍ የሚያሳዩበት መድረክ ነው። ለአመርቂ ስልጠና ደግሞ አመቺ የስልጠና ቦታ እጅግ ወሳኝ ነው። ቦታው ጨዋታውን የሚወክል ልምምድ የሚሰጥበት እና ለመጎልበት በቂ ሚና ሊጫወት የሚገባ መሆን አለበት።
የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች ሜዳ ሲገቡ የሚያደርጉት የ30 ወይም 40 እና 50ሺህ ብር ታኬታ ቢሆንም ልምምድ የሚሰሩት ግን ፎቶው ላይ በሚታየው እና አብዛኛውን ጊዜ በአትሌቲክስ በተለይም በጎዳና ላይ ሩጫ ወይም በጤና ቡድን ጨዋታዎች ላይ በተለመደው «ቶርሽን» ጫማ ነው። በዚህ ፍፁም እግር ኳሳዊ ባልሆነ ጫማ በሳምንት 5ቀን ልምምድ የሰራ ተጨዋች የጨዋታ እለት እንደሙሽራ በውድ ታኬታ ተውቦ እና አሸብርቆ ቢመጣ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እዚህ ጋር ተጨዋቾቹ ሜዳው የፈቀደላቸውን ጫማ መጫማታቸው የማያስወቅሳቸው ቢሆንም (እንዴውም ከጤናቸው አንፃር ትክክል ናቸው) ልምምዳችን እና ጨዋታችን ምን ያህል የተራራቁ እንደሆኑ ለማሳያ ይህ በራሱ በቂ አስረጂ ሆኖ ይቀርባል። ስለ ታክቲክ፥ ቴክኒክ፥ አካልብቃት እና ስነልቦና ሳናወራ ምን ያህል ደካማ የልምምድ እድል ለተጨዋቾቻችን እንደፈጠርን ለመረዳት ይህንን ፎቶ እና መከራከሪያ ነጥብ ማቅረብ ይበቃል። እንዲህ ፍፁም ምቹ ባልሆነ ሜዳ ላይ ልምምድ አሰርቶ ከጋዜጠኛው ፊት ስለ ታክቲክ የሚያወራ አሰልጣኝ፥ አሰላለፉ በዚህ ወጥቶ በዚህ ገብቶ የሚል ባለሙያ የሆነ የካደው ነገር ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤«ተገቢውን ልምምድ እየሰራን አይደለም» የሚል መልስ በቂ ይመስለኛል።
ዶሮን ስንዴ በትኖ ወዲያ ወዲህ በማሯሯጥ ስፖርተኛ ማድረግ እንደማይቻለው ሁሉ ተጨዋችንም ኳስ በትኖ ወዲያ ወዲህ በማድረግ ይሻሻላሉ ብሎ ማሰብ አላዋቂነት ነው። ስልጠና አካልም፥ አእምሮም፥ ጥበብም የሚዋሀድበት ልዩ ቦታ ነው፥ ስልጠና በምንም ነገር የሚተካ አይደለም። እንዴውም ጭራሽ ለክፋቱ የተሳሳተ ስልጠና አቅምን ያቀጭጫል፥ ችሎታን ያጠፋል የሚል አስተምህሮ በስፖርት ሳይንስ ውስጥ አለ። በስልጠና ያላገዝነውን ተጨዋች በኢንሴንቲቭ (በተጨዋቾች የቦነስ ክፍያ) ለማምጣት፥ በቦርድ ስብሰባ ለመፍጠር ከፍተኛ መጋጋጦች በእግር ኳሳችን ይታያሉ።
በእንደዚህ አይነት እግር ኳስ ሜዳ ላይ ተጨዋችን አበቃለሁ፥ ክለብን አሻሽላለሁ፥ አለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዲወክለኝ አደርጋለሁ ማለት በጀት በጅቱልኝ እንጂ፥ ብቻ እናንተ ገንዘቡን ስጡኝ እንጂ «አሳ ያለ ውሀ አረባለሁ» የማለትን ያህል ድፍረት ነው። አሳ ከውሀ ውጭ እንደማይኖረው ሁሉ ስፖርተኛንም ከልምምድ አርቆ ማሳደግ አይቻልም። ልምምድ ደግሞ በጤናማ ከባቢ ሁኔታ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ካልተደረገ እንደ እለታዊ ሪፖርት እንጂ እንደ ተግባራዊ ስራ አይቆጠርም። «ተከናውኗል» ለማለት እና ሒሳብ ለማወራረድ ካልሆነ በስተቀር በዚህ መልኩ የሚደረግ ስልጠና እና ልምምድ እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ የለውም። የኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ አቅም እና ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች የሚመክኑባቸው፥ እንደ ስፖርተኛ ፍፁም ለመለወጥ እና ለማደግ የማይመቹ ተቋማት ሆነዋል።
እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሚቀልድ እና የሚያፌዝ ሀገር እንደሌለ ይሄ ፎቶ ማረጋገጫ ነው። ይህ ፎቶ የአንድ የቅርጫት ኳስ አልያም የቮሊቮል ወይም የእጅ ኳስ ክለብ ፎቶ ቢሆን እንዲህ ተብሰልስዬ አስተያየቴን ለመፃፍ አይዳዳኝም ነበር። ምክንያቱም እነዚህ የስፖርት አይነቶች ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው፥ በቂ በጀት የማይበጀትላቸው፥ ለአደረጃጀት እና ለሪፖርት ብቻ የሚፈለጉ የስፖርት ዘርፎች በመሆናቸው ሰዎች ባላቸው ነገር መስራታቸውን አድንቄ ብቻ አልፈው ነበር። ይህ ፎቶ ግን ባለፉት አምስት አመታት ብቻ አስር ቢሊየን ብር ሊጠጋ የሚችል (የሊጉ የአመት ወጪ 2 ቢሊየን ብር ነው የሚል መረጃ በተለያዩ መልኩ ቀርቧል) የህዝብ ሀብትን ያጠፉ እና ያወደሙ፥ በእግር ኳሱ ውስጥ ምንም አይነት አሻራ የሌላቸውን፥ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር ምንም አይነት ልማት ያላወረሱ ክለቦችን የሚወክል በመሆኑ አንድም እንደ ግብር ከፋይ የመዘረፍ አለፍ ሲልም እንደ ባለሙያ ደግሞ የመበደል ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።
እግር ኳስ ልማት ነው፥ እግር ኳስ ኢንቨስትመነት ነው፥ እግር ኳስ ኢንዱስትሪ ነው የሚሉት አረፍተ ነገሮች በእግር ኳስ ክለብ አመራሮቻችን ምላስ እና ከንፈር ላይ ብቻ የሚገኙ ተላምጠው ያልተዋጡ፥ ከሰውነት ጋር ያልተዋሀዱ፥ ወደ አእምሮ ዘልቀው ያልገቡ እሳቤዎች ናቸው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፍፁም ኢትዮጵያን የማይመስልበት እና ኢትዮጵያን የማይወክልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ- የኢትዮጵያ እግር ኳስን በአስተሳሰብም ሆነ በአርቆ አሳቢነት ጥላው ከሄደች ቆይታለች። የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንኳን የስፔን፥ የብራዚል፥ የእንግሊዝ፥ የግብፅ፥ የናይጄሪያ፥ የሞሮኮ እግር ኳስ ጋር ሊፎካከር ቀርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሌሎች የልማት ወይም የንግድ አስተሳሰቦች የሚወዳደርበት አድማስ የለውም። «ቀጣይ ከማን ነን?» ከሚል ስትራቴጂ የለሽ ጥያቄ ውጭ መጋጠም፥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ብቻ አጀንዳ በሆነበት እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ነገር ለማሰብ የአእምሮ አቅሙም ሆነ አድማሱ፥ ችሎታውም ሆነ እውቀቱ፥ ፍላጎቱም ሆነ ተነሳሽነቱ የለም። በተለይ በክለቦች ውስጥ የሚታየው እጅግ ኋላ ቀርነት ካለማወቅ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም እግር ኳስን አቃሎ እና አቅልሎ ከማየት፥ ሌላ ጊዜም ትውልዱን እና ታናናሾቻቸውን ከመናቅ፥ ባስ ሲልም ኢትዮጵያን ካለመውደድ እና ከመጥላት የመነጨ እስኪያስመስል ድረስ የሚያስተዛዝብ ሆኗል።
አሁን ላይ የግል ባንኮቻችንን ዘመናዊነት እና እሳቤ ከክለቦቻችን ጋር ማወዳደር የማይታሰብ ነው፤ ክለቦቻችን ቦሌ አካባቢ የሚገኝ ካፌ እና ሬስቶራንት ያለውን ያህል ራዕይ የላቸውም፥ በዛም ደረጃ ስራቸውን ጥንቅቅ አድርገው ለመስራት ሲተጉ አይታዩም። ዛሬ ሸሚዝ እና ሱሪ የሚሸጡ ቡቲኮች ከክለቦቻችን በላይ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሀብት አላቸው። መካከለኛ ገቢ ያለው አንድ የመርካቶ ነጋዴ አያዋጡትም እንጂ ክለቦችን ለመግዛት የሚያስችል የፋይናንስ አቅም አለው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች እግር ኳስን የሚያህል ኢንዱስትሪ ውስጥ ለስንት አስርት አመታት ተቀምጠው፥ አለም አቀፍ ይዘት ያለው ዘርፍ ውስጥ ሆነው፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ከጀርባቸው አድርገው፥ በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ በየአመቱ ፈሰስ እየተደረገላቸው፥ አንድ ትላንት ወደ መድረክ ብቅ ካለ በዛም በዚህም ብሎ የራሱን ተከታይ ካፈራ «ቲክቶከር» ያነሰ ሐብት እንዳላቸው ማሰብ በእጅጉ ያማል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 15 አመታት በክለቦቿ በኩል ያድፋፋችውን ገንዘብ በስልት እና በስትራቴጂ በተደገፈ የእግር ኳስ ልማት/ ኢንቨስትመንት ላይ አውላው ቢሆን ኖሮ በአንድ ከተማ ላይ አራት እና አምስት የተንጣለሉ የክለብ የስልጠና ማዕከላት እና የልምምድ ሜዳዎች ሊኖሩን በተገባ እና ዛሬ ልጆቻችን እንዲህ ባለ ሜዳ ላይ ልምምድ እንዲሰሩ ባላስገደድናቸው ነበር። አሁንም ይሄንኑ ነውር እና ደካማ እንቅስቃሴ በማስቀጠል ቀጣዩ ትውልድም የእግር ኳስ ልማት አልቦ ውስጥ ለመክተት ሽር ጉድ ማለቱን ተያይዘነዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ባለፉት 15 አመታት ስላባከኑት እና ደብዛውን ስላጠፉት የግብር ከፋዩ ገንዘብ ኢትዮጵያን፣ የኢትዮጵያ ህዝብን እና የኢትዮጵያ መንግሥትን ይቅርታ ሊጠይቁ እና በዚህ ሂደት ውስጥም መሪ ተዋናይ የነበሩትን እና በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እዚህ ቅርቃር ውስጥ የከተቱንን ሰዎቻቸውን ንሰሀ እንዲገቡ «ሊያነቋቋቸው» ይገባል።
ስለፀሐፊው
ፀሐፊው ሳሙኤል ስለሺ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል የእግር ኳስ እና የስፖርት ስነልቦና መምህር ሲሆኑ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። በአሁኑ ሰዓትም በጀርመን ስፖርት ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ስፖርት ልማት እና ፖለቲካ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው።

