ሪፖርት | አዳማ ላይ የተካሄዱት የዕለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

ሪፖርት | አዳማ ላይ የተካሄዱት የዕለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

ወላይታ ድቻን ከ አርባ ምንጭ እንዲሁም መቐለ 70 እንደርታን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኙት የ12ኛ ሳምንት መክፈቻ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ወላይታ ድቻ ከ አርባ ምንጭ ከተማ

ጨዋታው ከጅማሮው አንስቶ በሁለቱም ቡድኖች በኩል መጠነኛ መዳከም የታየበት ነበር። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ጠንካራ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቡድኖቹ ተቸግረው የታዩ ሲሆን በ27ኛው ደቂቃ ላይ የአርባ ምንጩ በፍቅር ግዛቸው ከመስመር ቀጥታ የሞከረው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀረው ግን ወላይታ ድቻዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ዮናታን ኤልያስ ከሳጥኑ ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ጥረት ለጥቂት ወደ ውጭ ውጥቷል።

ከእረፍት መልስ አርባ ምንጮች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማሳየት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ነገር ግን 56ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ሙሉቀን አዲሱ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቷል።

በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ የጨዋታውን ብልጫ የወሰዱት ድቻዎች በ84ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የአርባ ምንጩ ተከላካይ አካሉ አቲሞ ለመከላከል ሲሞክር ወደ ራሱ ግብ የጨረፈው ሲሆን ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ ኦጎዶጆ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስመለክቱን 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጨዋታው በሁለቱም ወገኖች ተመጣጣኝ በሆነ የኳስ ቁጥጥር የጀመረ ሲሆን ገና በ16ኛው ደቂቃ ላይ መቐለ 70 እንደርታዎች በፍፁም  አለሙ የቅጣት ምት አማካኝነት የመጀመሪያውን አደገኛ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ከመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በኋላ ግን መቐለዎች ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የጀመሩ ሲሆን በ36ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ኳስን እየገፋ ወደ ሳጥን በመግባት ግብ ጠባቂውን ለማለፍ ቢሞክርም፣ የጊዮርጊስ ተከላካዮች በጊዜ ደርሰው አክሽፈውበታል።

በ39ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በረጅሙ የላከው ኳስ ለጥቂት በግብ አግዳሚው ላይ ወጥቷል። ሆኖም ከአንድ ደቂቃ በኋላ በ40ኛው ደቂቃ ላይ ተገኑ ተሾመ ከመስመር ሰንጥቆ በመግባት ያቀበለውን ኳስ አቤል ያለው ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ የአቻነት ግባቸውን ለማግኘት ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት መቐለዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ ከቦና ዓሊ የተቀበለውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ቢሞክረውም ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ላይ ወጥቶበታል።

ወደ ጨዋታ ለመመለስ አሁንም ጫናዎችን ፈጥረው መጫዎት የቻሉት ምዓም አናብስት በ80ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ ፍሬ ያፈሬበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከማዕዘን ምት የተላከውን ኳስ ተከላካዮች በአግባቡ ማጽዳት ሳይችሉ ቀርተው ያገኘውን ኳስ ተመስገን ተስፋዬ ግሩም በሆነ አጨራረስ ኳስና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።