መቐለ 70 እንደርታዎች ኢትዮጵያ መድንን አንድ ለባዶ በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን አሳክተዋ።
ኢትዮጵያ መድን እና መቐለ 70 እንደርታን ያገናኘው
የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ-ግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ ከፍፁም ዓለሙ በሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ምዓም አናብስቶች ብልጫ የወሰዱበት ነበር።

የተሻለ ጫና ፈጥረው ፍፁም ዓለሙ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ተጫዋች አታሎ መቷት ፋሲል ገብረሚካኤል በጥሩ መንገድ ባዳናት ለግብ የቀረበች ሙከራ ጥቃታቸውን የጀመሩት መቐለ 70 እንደርታዎች በ25ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ እና ፍፁም ዓለሙ ተቀባብለው ሙልጌታ ወደ ሳጥን ይዟት ገብቶ አሻግሯት ያሬድ ካሳዬ በአግባቡ ያላራቃትን ኳስ ፍፁም ዓለሙ ከግቡ አፋፍ መቶ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ምዓም አናብስትን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ ነበረች።
በአጋማሹ የተቀዛቀዘ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው መድኖችም ከመስመር ተሻምታ ብሩክ ሙልጌታ በግንባሩ ካደረጋት ሙከራ በኋላ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ሙከራዎችን ሳያደርጉ ቢቆዩም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ዳዊት አውላቸው ከተከላካይ ጀርባ አሻግሯት ወገኔ ገዛኸኝ የመቐለ 70 እንደርታ ተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ከተገናኘ በኋላ መረጋጋት ተስኖት ያመከናት ኳስም መድኖችን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች።

ኢትዮጵያ መድኖች የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ መድኖች ደግሞ የአቻነት ግብ ፍለጋ ባደረጉት ፍልምያ የታጀበ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር።
በአጋማሹ በብዙ ረገድ ተሻሽለው የቀረቡት መድኖች የመቐለ 70 እንደርታን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ተቸግረው ከቆዩ በኋላም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ብሩክ ሙሉጌታ 81ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ ከግቡ አፋፍ ሆኖ በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት እንዲሁም ያሬድ ካሳዬ ሳጥን ውስጥ ነፃ ለነበረው አለን ካይዋ አቀብሎት ዩጋንዳዊው አጥቂ ከግቡ አፋፍ ሆኖ መቷት መሐመድ ዛግዩ የመለሳት ኳስም የማታ ማታ መድኖችን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ። በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታም የፍፁም ዓለሙ ብቸኛ ግብ ምዓም አናብስትን አሸናፊ አድርጋለች።

