መረጃዎች | የ14ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ14ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

14ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ መርሐግብሮች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሽረ ምድረገነት ከ ነገሌ አርሲ

በ17 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሽረ ምድረ ገነት ነጥቡን 20 አድርሶ ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለማለት ከጠንካራውን ነጌሌ አርሲ ጋር ይፋለማል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ኢትዮጵያ ቡናን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ ከአራት መርሐግብሮች በኋላ ድል ያደረጉት ሽረዎች በዛሬው ፍልሚያ ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ የነበራቸው ውጤታማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ማስቀጠል እና ለተጋጣሚያቸው ፈጣን ሽግግሮች በብቁ መንገድ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

በ22 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ክስተቱ ነገሌ አርሲ መሪዎቹን በቅርበት ለመከታተል የሚያስችለው ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባል። በመጨረሻው መርሐግብር መቻልን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ያሳካው ቡድኑ በ10ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ በተካሄዱት ጨዋታዎች እጅ አልሰጠም። መረባቸውን ሳያስደፍሩ ስድስት ግቦች ባስቆጠሩባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ያሳዩት ድንቅ እንቅስቃሴ ማስቀጠልም የአሰልጣኝ ቱሉ ደስታ ብቸኛው ሥራ ይሆናል።

ሽረ ምድረገነት በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች የለም። ነገሌ አርሲዎች ግን ዛሬም ጉዳት ላይ የነበሩትን አብዱልበሲጥ ከማል፣ በረከት ወልዴ፣ ኢብሳ በፍቃዱ እና ገብረመስቀል ዱባለን ግልጋሎት  አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ በታሪካቸው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ያከናውናሉ።

ሲዳማ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

በ28 ነጥቦች በሊጉ አናት የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች መሪነታቸውን ለማጠናከር በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘውን አርባምንጭ ከተማ ይገጥማሉ።

በመጨረሻው ሳምንት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን በማሸነፍ ከተከታያቸው ፋሲል ከነማ ያላቸውን የነጥብ ልዩነቱን ከፍ ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መልስ ድል ባደረጉባቸው ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ያሳዩት መሻሻል ድንቅ ነበር። በዛሬው ጨዋታም በተለይም በፊት መስመር ተጫዋቾች ላይ የሚታየውን ጥሩ ተግባቦት ማስቀጠል ከአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ቡድን ይጠበቃል።

በ7 ነጥብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ከስጋት ቀጠናው ለመውጣት ተስፋ የሚያሰንቃቸውን ነጥብ ለማግኘት ከሊጉ መሪ ይፋለማሉ። አዞዎቹ በአስራ ሦስት ሳምንታት ጉዞ ድል ማስመዝገብ አልቻሉም። ቡድኑ ምንም እንኳን ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም ከደካማው አጀማመር ቀና ለማለት ድል ማድረግ ግድ ይለዋል። ይህ እንዲሳካ ደግሞ በ13 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን በብዙ ረገድ ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

ሲዳማ ቡናዎች በዛሬው ጨዋታ አምስት ቢጫ ካርዶችን የተመለከተውን አጥቂያቸው መስፍን ታፈሰ ግልጋሎት አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ19 ጊዜያት ተገናኝተው 13 ጨዋታዎች አቻ ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ 4 ሲዳማ ቡና ደግሞ 2 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ አዳማ ከተማ

10 ነጥቦች ሰብስበው 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ካሉበት የአደጋ ክልል የሚያላቅቅ ድል ፍለጋ አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።

በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከባህርዳር ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ የተጋሩት ቢጫዎቹ በቅርብ ሳምንታት በአወንታነት የሚጠቀሱ መሻሻሎች አሳይተዋል። ቡድኑ በ8ኛው እና 9ኛው ሳምንት ተከታታይ ድሎች ማሳካቱ እንዲሁም በመጀመራያዎቹ 7 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ በመጨረሻዎቹ 6 መርሐግብሮች መሻሻል አሳይቶ 3 ግቦችን ብቻ ማስተናገዱም የዚህ ማሳያ ነው። ሆኖም በዛሬው ጨዋታ ድል አስመዝግቦ ደረጃውን ለማሻሻል የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።

በ21 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ወደ መሪዎቹ የሚጠጉበትን ዕድል ለማመቻቸት ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። በ13ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በሊጉ ሁለት ሽንፈቶችን ብቻ ቢያስተናግድም
በ13 ሳምንታት ጉዞ ውስጥ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ የቻለው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነበር። ከዚህ ወጥነት የጎደለው አካሄዱ ለመላቀቅም በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የተሳነውን የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ማሻሻል ይኖርበታል።

ወልዋሎዎች በመጨረሻው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ሙሉዓለም መስፍንን አያሰልፉም ፤ ፍቃዱ መኮንን ግን አገግሞ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በአዳማ ከተማ በኩል ከኢዮብ ማቲያስ እና ዳዋ ሆጤሳ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ የወጣውን መናፍ ዐወል ግልጋሎት አያገኙም።

በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 6 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 3 ሲያሸንፍ፣ ወልዋሎ አንድ አሸንፎ ሁለቱን ጨዋታዎች አቻ ተለያይለዋል። አዳማ 9፣ ወልዋሎ 3 አስቆጥረዋል።