በአ/ሳ/ቴ/ዩ በተካሄዱ ጨዋታዎች ሰጎኖቹ እና የጦና ንቦቹ 1ለ1 ሲለያዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ1 አሸንፏል።

ነጌሌ አርሲ ከ ወላይታ ድቻ
በዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ መሪነት በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ነጌሌዎች መጠነኛ ብልጫ ሲወስዱ በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ግን ወላይታ ድቻዎች የተሻሉ ነበሩ።
ብዙም ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት አጋማሽ ድቻዎች በያሬድ ዳርዛ እና በቴዎድሮስ ኃይለማርያም አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ጠባቂውን ኢድሪሱ አብዱላሂን መፈተን አልቻሉም ነበር። ነጌሌዎች በአንጻሩ አንድም የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ 48ኛው ደቂቃ ላይ የጦና ንቦች ጎል የሚያስቆጥሩበት ወርቃማ ዕድል አግኝተው ዮናታን ኤልያስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ ኳሱን ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ መልሶበታል።
ከወትሮው በተለየ ተዳክመው የቀረቡት ሰጎኖቹ በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራቸው ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ካቤ ብዙነህ ከሳጥን አጠገብ ራሱ ላይ በተሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ቢመታውም የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።
ወላይታ ድቻዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ሙከራቸውን ሲያደርጉ ቅዱስ ቂርቆስ ከበፍቃዱ ሕዝቅኤል በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ ተቸግረው የነበሩት ነጌሌ አርሲዎች 83ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ አስቆጥረዋል። ዳዊት ተፈራ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ወደ ሩቁ ቋሚ ያሻገረውን ኳስ ሮሆቦት ሰላሎ ገጭቶ ወደመሃል መልሶት ያንን ኳስ ያገኘው ገብረመስቀል ዱባለ በግንባሩ በመግጨት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 5 ደቂቃዎች ውስጥ አራተኛው ደቂቃ ላይ የጦና ንቦቹ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ብሩክ ኤልያስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ኳሱን ወደ ውስጥ ሲያሻግር ተከላካዩ ቦና ቦካ ኳስ በእጁ ነክቷል በሚል የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ኳሱን ጎል አድርጎታል። ጨዋታውም 1ለ1 ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በዋና ዳኛ ዓባይነህ ሙላት መሪነት በተካሄደው የምሽት 12 ሰዓት ጨዋታ ኤሌክትሪኮች ገና በ6ኛው ደቂቃ መሪ መሆን የቻሉበት ነበር። ኢዮብ ገብረማርያም ከአሸናፊ ጥሩነህ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ በድንቅ ሁኔታ በመምታት ግብ አስቆጥሯል።
የአቻነት ግብ ፍለጋ ሲታትሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 19ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሁዘይፋ ሻፊ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሳይመን ፒተር በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው የሱፍ ሞሩ በድንቅ ብቃት አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ፉክክሩ ተሻሽሎ ሲቀጥል 48ኛው ደቂቃ ላይ ግን በጨዋታው አስደንጋጭ ክስተት ተፈጥሮ ነበር። የንግድ ባንኩ ኢብሳ ኩመራ መሬት ላይ በፊቱ በመውደቁ እና ምላስ በመዋጡ ምክንያት አፋጣኝ ሕክምና ሜዳ ላይ ቢደረግለትም ለተሻለ ሕክምና በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አምርቷል።
በጨዋታው መሪ ቢሆኑም በሚያገኟቸው ኳሶች ወደፊት የመሄድ ፍላጎት የነበራቸው ኤሌክትሪኮች 66ኛው ደቂቃ ላይም ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው ሀሰን ሁሴን ከሀብታሙ ሸዋለም በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወጥቶበታል።
ከዚህ ሙከራ የተረፉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግብ አስቆጥረዋል። አዲስ ግደይ ከቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ካሳሁን ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በግሩም ሁኔታ ከቅርቡ ቋሚ ላይ ሆኖ የመታው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል።
በጋለ ፉክክር እየቀጠለ በሄደው ጨዋታ ኤሌክትሪኮች በድጋሚ መሪ የሆኑበት ግብ 73ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ያሬድ የማነ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሀሰን ሁሴን በግንባሩ በመግጨት በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮታል። ከዚህ ግብ በኋላም ፉክክሮች ቢያይሉም ተጨማሪ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

