መቻል ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ያለ ግብ ተለያይተዋል

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
በአዲስ አበባ ስታድየም የተካሄደው የዕለቱ ቀዳሚ
ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራዎች ያልታጀበ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር።
በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ ረገድም ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያ መድኖች ሲሆኑ አለን ካይዋ በጨዋታው ጅማሮ ላይ የድሬዳዋ ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ወደ ግብ የሞከረው እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣው ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ነበር። መድኖች ከተጠቀሰው አጋጣሚ በተጨማሪ በወገኔ ገዛኸኝ አማካኝነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ካደረጉ በኋላም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ወገኔ ገዛህኝ ከመስመር አሻግሮት በነፃ አቋቋም፣ ከግቡ አፋፍ የነበረው ረመዳን የሱፍ በማይታመን መልኩ ወደ ግብነት ያልቀየረውና ዒላማውን ያልጠበቀው ሙከራም በአጋማሹ የታየ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት እንዲሁም ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉበት ነበር።
በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች በተፈጠሩበት አጋማሽም በኢትዮጵያ መድን በኩል ያሬድ ካሳየ ከቆመ ኳስ አሻምቷት በረከት ካሌብ በግምባሩ ከገጫት በኋላ ፍሬው ጌታሁን እንደምንም ያወጣት እንዲሁም ብሩክ ሙልጌታ አሻምቷት አለን ካይዋ በግምባሩ ያደረጋት እና በረመዳን የሱፍ አማካኝነት የተደረገች ሙከራ ተጠቃሾች ሲሆኑ በድሬዳዋ ከተማ በኩልም ጃዕፈር ሙደሲር ከግቡ አፋፍ አከባቢ ከፍ አድርጎ መቷት ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ እና ዘርአይ ገ/ስላሴ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም አብዱላሂ ጋንዩ ኳስ ለማውጣት ሲሞክር ወደ ራሱ ግብ መቷት የግብን ቋሚ ገጭታ የተመለሰች ኳስ ብርቱካናማዎቹን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።
ሁለት የተለያየ መልክ የነበራቸው አጋማሾች ያስመከለተን ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
መቻል ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡትን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መቻሎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን ጳውሎስ ከንቲባ መትቷ ለጥቂት የወጣችው ሙከራም የመጀመሪያዋ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።
መቻሎች በአጋማሹ የተሻለ የፊት መስመር እንቅስቃሴ በማድረግ በረከት ደስታ አሻምቶት ቸርነት ጉግሳ በግምባር ባደረገው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ካደረጉ በኋላም በ28ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። ፈቱዲን ጀማል ከቅጣት ምት ተሻምቶ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡትን ኳስ ከረዥም ርቀት አክርሮ በመምታት ያስቆጠረው አስደናቂ ግብም ጦሩን መሪ አድርጓል። መቻሎች የመጀመሪያውን ግብ ካስቆጠሩ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም መሪነታቸውን ያጠናከሩ ሲሆን ፈቱዲን ጀማል ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሀያ አምስት ያህል ደቂቃዎችም ይሄ ነው የሚባል ሙከራ አልተደረገም።
በረዣዥም ኳሶች ግቦችን አስቆጥረው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ባደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ75ኛው ደቂቃ ላይ ቶሎሳ ንጉሴ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ጥሩ በሆነ ቅልጥፍና ያወጣው እንዲሁም ፍፁም ጥላሁን በድጋሜ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረገው ሙከራም በአጋማሹ የታዩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው። ጨዋታውም ተጨማሪ ግቦችን ሳያስተናግድ በመቻል 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

