የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት የመዝጊያ ጨዋታ ዛሬ ሲደረግ ምዓም አናብስቶች በስንታየሁ መንግስቱ ብቸኛ ግብ ምድረ ገነት ሽረን አሸንፈዋል።

የሰሜን ክለቦችን ባገናኘው የሳምንቱ የመዝጊያ መርሃ ግብር በኳስ እንቅስቃሴ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር አስመልክተውናል። የሜዳው የመሀል ክፍል ላይ ኳሶች በብዛት ይቆራረጡ በነበረበት አጋማሽ በምድረ ገነት ሽረ በኩል ዳንኤል ዳርጌ ወደግብ መቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት እንዲሁም በመቐለ በኩል ስንታየው መንግስቱ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ካባከነው ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ መቐለ 70 እንደርታዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም አለሙ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህም በውድድሩ ዘመኑ የመጀመሪያው የሊግ ግቡ ተደርጎ በስሙ ተመዝግቦለታል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ምድረ ገነት ሽረዎች በይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በዳንኤል ዳርጌ፣ አቤል ማሙሽ እንዲሁም በስንታየው ዋለጨ ቅጣት ምት እንዲሁም በመቐለ 70 እንደርታ በኩል በደስታ ዮሐንስ አማካኝነት ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት መቐለ እንደርታዎች ማሸነፍ ችለዋል።

