ሲዳማ ቡና መሪነቱን ያስቀጠለበት ወሳኝ ድል ተጎናፀፈ

በበርካታ የሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ በተደረገው 32ኛው የሮድዋ ደርቢ በክለቦቹ መቀመጫ በሆነው ሀዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን አድርገዋል። ከደርቢ ስሜቱ በተጨማሪ የሊጉን መሪነት ለመረከብ እና መሪነትን ለማፅናት ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል እጅግ ወኔ የተሞላበትና ለመሸናነፍ ከፍተኛ ትንቅንቅ የተደረገበት አጋማሽ ነበር።
የግብ ሙከራዎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባዬ ሞክሮት የግቡ ቋሚ ከመለሰበት ሙከራ በኋላ የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 43ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ በግራ መስመር ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ብርሃኑ በቀለ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተጨዋች ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሀዋሳ ከተማዎች አጋማሹ በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ነጥቆ ወደ ሳጥን በመግባት አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ መሬት ለመሬት መቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ነገር ግን ሀዋሳ ከተማዎች ደስታቸው መዝለቅ የቻለው ለአራት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 53ኛው ደቂቃ ላይ ደግፌ አለሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ መስፍን ታፈሰ መስፍን በግንባሩ ገጭቶ በቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ በማስመዝገብ ቡድኑን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሀዋሳዎች ጫናዎችን በመፍጠር 80ኛው ደቂቃ ላይ የግቡ አግዳሚ በመለሰባቸው የጌታነህ ከበደ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም የሲዳማን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው የስድስት ነጥብ ያክል ተጠባቂ የነበረው የደርቢ ጨዋታ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።

