ነገሌ አርሲዎች በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ
አዳማ ከተማን 2 ለ 1 በማሸነፍ ጣፋጭ ድል ተቀዳጁ
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ባስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ 23ኛው ደቂቃ ላይ በነገሌ አርሲ በኩል ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጭ ሞክሮ በግቡ አግዳሚ ከወጣበት እንዲሁም 42ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው አህመድ ሁሴን ሞክሮ ግብ ጠባቂው እድሪሱ አብዱላሂ ከመለሰበት የግብ ሙከራዎች ውጪ ሌላ የግብ እድሎችን ሳንመለከት ጨዋታው አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ 51ኛው ደቂቃ ላይ ነገሌ አርሲዎች በሳጥኑ ግማሽ ጨረቃ ላይ ያገኙትን የቆመ ኳስ የቅጣት ምቱ ስፔሻሊስት የሆነው ዳዊት ተፈራ በቀጥታ መቶ በአስደናቂ ሁኔታ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በፈጣን ሽግግር የታጀበ እና ፋታ የለሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በ79ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ዳዋ ሆቴሳ ግሩም በሆነ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማን አቻ አድርጓል። ጎሉም የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ግብ ተደርጎ ተመዝግቦለታል።

መደበኛው የጨዋታ ሰዓት እንዲሁም የተጨመሩ ደቂቃዎች ተጠናቀው ዳኛው ፍጻሜውን በፊሽካ ለማብሰር ሲጠባበቁ የነጌሌ አርሲው ተጫዋች ሮበርት ሰላሎ ፤ ዳዊት ተፈራ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን የማታ ማታ አሸናፊ ያደረገች ወሳኝ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ባለ ድል አድርጓል።


