የ26ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች !

ባህርዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ
ሰላሣ ሁለት ነጥቦች ሰብስበው ከተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ዝቅ ብለው 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ሁለት ደረጃዎችን ለማሻሻል የሚረዳቸውን ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።
ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የ25ኛው ሳምንት ጨዋታ መልስ የሁለተኛው መንፈቅ ሦስተኛ ድላቸውን ለማግኘት የሚፋለሙት የጣና ሞገዶቹ አራት ግቦች ካስተናገዱባቸው ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ከሽንፈት መራቃቸው እንዲሁም በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረባቸውን ማስከበራቸው እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ነጥብ ቢሆንም የግብ ማስቆጥር ችግራቸውን በዘላቂነት መፍታት አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ ኳስና መረብ ያላገናኘው እና ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ ከአንተነህ ተፈራ ዝውውር በኋላ ተስፋ ሰጪ ለውጦች ማሳየት ቢችልም ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በማጥቃቱ ረገድ ያሉበትን ክፍተቶች ማረም ይኖርበታል።
በሰላሣ ሦስት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከአስከፊው የሁለተኛ ዙር አካሄዳቸው ለመውጣት ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።
በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ሽንፈት ያስተናገደው አዳማ ከተማ በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው ውጤቶች ከነበረበት የሰንጠረዡ ወገብ ተንሸራቶ አካፈዩ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት፣ ሁለት አቻ እና አንድ ድል አስመዝግቦ ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ አምስቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ከዚህ አካሄድ ለመላቀቅ በርከት ያሉ ለውጦች ማድረግ ግድ ይለዋል። በተለይም ከዘህ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረው እና ባለፉት አምስት መርሐ ግብሮች ብቻ አስራ አንድ ግቦችን ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ የወቅቱ የቡድኑ ቀንደኛ ድክመት ነው። ለተጠቀሰው ችግር መፍትሔ ማበጀትም የአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ ቀዳሚ የቤት ስራ መሆን ይገባዋል።
ባህርዳር ከተማ ባለፈው ሳምንት በጉዳት ምክንያት ያልነበረው አጥቂው ክዋቤና ቡአቲንግን ጨምሮ ሀሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ሆነውለታል።
የአዳማ ከተማን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነት ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 7 በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አዳማ 5 አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። ባህር ዳር 13 ሲያስቆጥር አዳማ 9 አስቆጥሯል።
ሲዳማ ቡና ከ መቻል
በመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ከተስተዋሉበት መቀዛቀዞች አገግሞ ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ በአርባ ስምንት ነጥብ በሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 9 ከፍ የሚያደርግበት ድል ለማግኘት ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናል።
በመጨረሻው ጨዋታ በአቤል ያለው ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታን አንድ ለባዶ በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ከፍ ያደረገው ሲዳማ ቡና በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መሻሻል በማስመዝገብ ኮስታራ የዋንጫ ቡድን መሆኑ እያሳየ ይገኛል። በሁለተኛው መንፈቅ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች አራት ድል፣ አንድ አቻና አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ የቅርብ ተፎካካሪዎቹ መዳከም በአግባቡ እየተጠቀመ የሚገኘው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ያሳየው ብቃት እንዲሁም ያስመዘገበው ውጤት በጥሩ ጎን የሚነሳለት ነጥብ ሲሆን የዋንጫ መንገዱ ይበልጥ ለማደላደል በፊት መስመር የሚስተዋሉበትን ውስን የአፈፃፀም እና የውሳኔ አሰጣጥ ድክመቶች መቅረፍ አለበት።
በጥራት ላቅ ያለ እንዲሁም ብዙ አማራጮች ያሉት የአጥቂ ክፍላቸው ውጤታማነት ከፍ በማድረግ ከመጨረሻዎቹ አራት ድሎች በሦስቱ በአንድ የግብ ልዩነት ብቻ ያሸነፈውን ቡድናቸው በምቾት ጨዋታዎችን እንዲያሸንፍ የሚያስችሉ ስራዎች መስራትም ከአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ይጠበቃል።
በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻል ነጥቡን 40 አድርሶ 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የሚያስችለውና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የሚቀላቅለውን ድል ለማግኘት የሊጉን መሪ ይገጥማል።
በሀያ ሁለተኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሁለት ለባዶ ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ድል ማድረግ ያልቻለውና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው መቻል ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ካስገኙለት ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ከነበረበት የመሪዎች ጎራ እንዲርቅ አድርገውታል። ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ ከዚህ አካሄድ ለመውጣትም በቀዳሚነት የፊት መስመሩን ጉልህ የአፈፃፀም ድክመት ማረም ግድ ይለዋል።
ቡድኑ በተከታታይ ነጥብ በተጋራባቸው ሦስት ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎቹ በተሻለ የግብ ዕድሎች ፈጥሮ ሙከራዎች ማድረግ ቢችልም የአፈፃፀም ድክመቱ ከአንድ ግብ በላይ እንዳይስቆጥር አድርጎታል። በዛሬው ጨዋታ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስም ለጠንካራው የተጋጣሚው የኋላ ክፍል በሚመጥን አኳኋን መቅረብ እና በቅርብ ሳምንታት በጥሩ ብቃት ያለውን የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 29 ጊዜ ሲገናኙ ሲዳማ ቡና 11 መቻል ደግሞ 10 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገዋል፤ 8 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 31፣ ሲዳማ 28 ጎሎች አስቆጥረዋል።

