ሪፖርት| ምዓም አናብስት ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል

ሪፖርት| ምዓም አናብስት ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል

መቐለ 70 እንደርታ በፍፁም ዓለሙ እና ዓብዱለጢፍ ባምባ ግቦች ታግዞ ወልዋሎ ዓ/ዩን 2 ለ 1 ረቷል

ገና በጨዋታው ጅማሮ ግብ ባስመለከተን ጨዋታ 3ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን እና ግብ ጠባቂው በአግባቡ ያላራቀውን ኳስ ያገኘውን ብርሃኑ አዳሙ ወደ ግብ ሞክሮት ተከላካዩ ነፃነት ገ/መድህን መስመር ላይ ደርሶ ማዳን ቢችልም ያንን ያዳነውን ኳስ በነጻ አቋቋም ላይ የነበረው ፍፁም ዓለሙ ወደ ግብነት ቀይሮ መቐለ 70 እንደርታዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጫናዎችን ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ወልዋሎዎች በፍሬው ሰለሞን እና በሰመረ ሀፍታይ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርቷል። መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች የመቐለ ተጫዋች የሆነው ደስታ ዩሀንስ የግብ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት የወልዋሎው አፈወርቅ ሀይሉ መቶት ግብ ጠባቂው መሐመድ ዜግዩ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ 62ኛው ደቂቃ ላይ መቐለ 70 እንደርታዎች መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ግብ አስቆጥረዋል። ቦና አሊ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ዓብዱለጢፍ ባምባ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን በሁለት ግብ ልዩነት መሪ ማድረግ ችለዋል።

ግብ ከተቆጠረባቸው ከአንድ ደቂቃ በኋላ ወልዋሎዎች ፈጣን የሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። 63 ኛው ደቂቃ ላይ ኮንኮኒ ሀፍዝ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ገብሩ በግራ እግሩ በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱን የሰሜን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።