ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በአዲስ መንገድ ሊካሄድ ነው

ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በአዲስ መንገድ ሊካሄድ ነው

ሀገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከግብፅ ጋር እንደምታከናውን ይፋ ሆነ

ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ሊደረግ የሳምንታት እድሜ ብቻ የቀሩት ሲሆን በየዞኑ በተደረጉ የማጣሪያ ውድድሮች ቀዳሚ የሆኑ ብሔራዊ ቡድኖችም ዝግጅታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ከ22 ዓመታት በኋላ ለውድድሩ ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በአሠልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር እየተመራ ዝግጅቱን በጥሩ ሁኔታ እያከናወነ ይገኛል።

ቀድሞ ይደረጋል ከተባለበት ቀን ተገፍቶ ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 25 ደረስ የሚደረገው ይህ ውድድር እንደከዚህ ቀደሞቹ አህጉራዊ ውድድሮች ቡድኖች በተለያዩ ከተሞች እና ስታዲየሞች ተመድበው የሚያደርጉት ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የፌስቲቫል አይነት ስሜት እንዲኖረው ቡድኖች ጨዋታቸውንም ሆነ ልምምዳቸውን እንዲሁም አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚያደርጉባቸው ስፍራዎች በአንድ አካባቢ እንዲሆን በማድረግ የአብሮነት ስሜት እንዲኖር ማሰቡን ካፍ አስታውቋል።

በዚህም ከውድድሩ የመክፈቻ፣ የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች ውጪ ሁሉም ጨዋታዎች በሞሐመድ 5ኛ የእግርኳስ ኮምፕሌክስ እንደሚደረጉ ተመላክቷል።

በምድብ 1 ከአዘጋጇ ሞሮኮ፣ ግብፅ እና ቱኒዚያ ጋር የተደለደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ግንቦት 6 ከግብፅ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን ስታደርግ ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ ከአዘጋጇ ሞሮኮ ጋር ከዛም ግንቦት 11 ከቱኒዚያ ጋር የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዋን ታከናውናለች።

በውድድሩ ከምድባቸው የሚያልፉ 8 ቡድኖች በቀጥታ ሁለት ቡድኖች ደግሞ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ተለይተው ኳታር በምታዘጋጀው የፊፋ የ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ውድድር የሚያልፉ ይሆናል።