ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ሲመለሱ ባህርዳር ከተማና ወልዋሎ ዓ/ዩ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ገና በጅማሮው በሁለቱም አጋማሾች የተለያዩ ገጽታዎችን ያስመለከተ ነበር። ጨዋታው በ12ኛው ደቂቃ በረከት ጥጋቡ እና ስምዖን ማሩ ኳሷን ለመሻማት ባደረጉት ብርቱ ግብግብ ኳሷ ግፊቱን መቋቋም አቅቷት መፈንዳቷ የአጋማሹ አነጋጋሪ ክስተት ሆኖ አልፏል። ምንም እንኳ የመጀመሪያው አጋማሽ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ባይመዘገብበትም ወልዋሎዎች ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ የተሻለ ብልጫ አስመልክተውን ነበር።

ወልዋሎዎች የፈጠሯቸውን ወርቃማ ዕድሎች ሳይጠቀሙባቸው መቅረታቸው ግን እጅግ አስቆጪ ነበር። በተለይም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች ሲቀሩ ኤፍሬም ኃይለማርያም ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለግቡ እጅግ ቅርብ ከነበረበት ቦታ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ መመለሱ ለመሳት የሚከብድና መላውን የወልዋሎ ደጋፊ ያስቆጨ አጋጣሚ ሆኖ ተመዝግቧል።

በባህር ዳር ከተማ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ የታየው የፈጠራ ብቃት መሻሻል የጨዋታውን ሚዛን ወደ እነሱ አዘንብሎታል። ባህርዳሮች በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ የማጥቃት ፍላጎታቸውን ቢያሳዩም ጥራቱን የጠበቀና መረብ ላይ ሊያርፍ የሚችል ሙከራ ማግኘት ተስኗቸው ታይቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ትዕይንቶችን ሳያስመለክተን ያለ ምንም ግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከነማ
በአሳቴዩ ስታዲየም በምሽት የተካሄደው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በመብራት መቋረጥ ለደቂቃዎች ቢስተጓጎልም በኤሌክትሪኮች ብልጫ ተጀምሯል። በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ሲሆኑ ወደ ሳጥን ዘልቆ በመግባት ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች በመፍጠር ረገድ ሁለቱም ቡድኖች በታየባቸው ድክመት ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ፋሲል ከነማዎች መነቃቃት ቢያሳዩም በ59ኛው ደቂቃ ቤዛ መድን ከአቤል ሀብታሙ የተሰነጠቀለትን ኳስ ተከላካዩ ምኞት ደበበ ለመመለስ ሲሞክር በራሱ ጥረት ተጭኖ የቀማውን ኳስ ከመረብ አሳርፎ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጓል። ኤሌክትሪኮች ግፊታቸውን በመቀጠል በ84ኛው ደቂቃ አሸናፊ ጥሩነህ በቅርብ ርቀት ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድጓል።
የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሙከሪም ረሺድ የፋሲል ተከላካዮች በቅጡ ያላራቁትን ኳስ ከርቀት በደረቱ አብርዶ አስገራሚ ግብ አስቆጥሯል። ይህች ድንቅ ግብ የኤሌክትሪክን የበላይነት ከማረጋገጧም በላይ የተጋጣሚያቸውን የተስፋ ብርሃን ይበልጥ ያጨለመች ክስተት ሆና አልፋለች።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ ፋሲል ከነማዎች በሳጥን ውስጥ የተገኘን የፍጹም ቅጣት ምት በበረከት ግዛው አማካኝነት አስቆጥረው መሪነቱን ማጥበብ ችለዋል። ሆኖም ጨዋታው 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቆ ቡድኑ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በታላቅ ድል ወደ ግስጋሴው ተመልሷል።

