የሊጉ መሪ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያሰፋበትን እድል በሸገር ከተማ 1ለ0 በመሸነፍ ሳይጠቀም ሲቀር እጅግ ማራኪ በነበረው ጨዋታ የጦና ንቦች አዞዎችን 3ለ2 በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

ሸገር ከተማ ከሲዳማ ቡና
ሸገር ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ቀዳሚው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ቡድኖቹ ቀዳሚ ለመሆን በሚያደርጉት ተደጋጋሚ ፈጣን ሽግግር እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ግለቱ ከደቂቃ ደቂቃ እየጨመረ ሲሄድ፤ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል በመድረስ አኳያ ጥሩ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም የሚያገኙትን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት ለመቀየር ሲቸገሩ እያስተዋልን በአንድ አጋጣሚ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ ብለስ ናጎህ ከሱራፌል ዳኛቸው የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ባሕሩ ነጋሽ እንዴትም ጨርፎ ያወጣባቸው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረበ ነበር።

ዮሴፍ ታረቀኝ የጨዋታ ጅማሮ ላይ በቆመ ኳስ ሙከራ አድርጎ ተጨርፎ ከወጣባቸው አጋጣሚ በኋላ ረዘም ላለ ደቂቃ ሙከራ ሳያስመለክቱን የቆዩት ሸገሮች ቢኒያም ፍቅሩ የቆመ ኳስ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ካገደበት በኋላ 32ኛው ደቂቃ ላይ ከቡልቻ ሹራ የተሻገረውን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ አሻምቶት ራሱ ቢኒያም ፍቅሩ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር መሪ አድርጓቸዋል። አጋማሹ ለሸገሮች የግብ ብልጫ በማስገኘት እንዲሁ የሲዳማ ቡናዎች የጨዋታ ብልጫ በማስመልከት ተገባዷል።

በሲዳማ ቡና የኳስ ቁጥጥር እና ጫና በተመለሰው በሁለተኛው አጋማሽ በሙሉ ኃይላቸው ለማጥቃት ወደ ተቃራኒ ቡድን እየገቡ ተከላካዮችን መፈተን የቻሉ ቢሆንም የጠራ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። በመልሶ ማጥቃት ይገቡ የነበሩት ሸገሮች ሚሊዮን ኃይሉ መትቶ የቋሚ ብረት መልሶበት ድጋሚ ራሱን ኳስ ቢኒያም ፍቅሩ አግኝቶ አክርሮ መትቶ ብርሃኑ በቀለ ከመስመር የመለሰበት አጋጣሚ መሪነታቸው ከፍ ለማድረግ እጅጉን የተቃረበ አደገኛው ሙከራ የነበረ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሸገር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አርባምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻ
አዞዎቹን ከጦና ንቦች ያገናኘው ሁለተኛው ከደጋፊዎች ጋር ታጅቦ የተደረገው ጨዋታ በጦና ንቦች የበላይነት ጅማሮውን ማድረግ የቻለ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የነበራቸውን ብልጫ ተጠቅመው መሪ መሆንም ችለዋል፤ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከራሳቸው ሜዳ መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መሳይ ሰለሞን ረጅም ርቀት ኳሱን እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ 14ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
አዞዎቹ የአቻነት ግብ አግኝተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ በሚያደርጉት እንቅሰቃሴ የኳስ ቁጥጥር መውሰድ የቻሉ ቢሆንም ኤፍሬም ታምራት በቆመ ኳስ አድርጎ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ካወጣባቸው ሙከራ ውጨ አደገኛ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። ይልቁንም ወላይታ ድቻዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የቀረቡበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል፤ ከእነዚህም መካከል መሳይ ሰለሞን ቴዎድሮስ ታፈሰ ወደ ሳጥን ያሻገረለትን ኳስ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ በደካማ አጨራረስ ያመከነበት አስቆጪው አጋጣሚ ሲጠቀስ አጋማሹም በአዞዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተገባዶ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ከተጨማሪ ግብ ፍለጋ ተነሳሽነት ጋር የተመለሱት የጦና ንቦች 59ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪው አጋጣሚ በአንድ ደቂቃ ልዩነት የአዞዎቹ ግብ ጠባቂ ከግቡ ለቆ ወጥቶ ኳሱን ሲያርቅ መሃል ሜዳ ላይ ኳሱን ያገኘው ሙሉቀን አዲሱ ቀጥታ ወደግብ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን አጠናክሯል። በዚህ ብቻ ያላበቃው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ሦስተኛውን ግብ አስገኝቶላቸዋል። መሳይ ሰለሞን 70ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ሌላኛውን ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

ጨዋታው ወደ መጨረሻው ደቂቃ ሲያመራ የተነቃቁት አዞዎቹ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ፍለጋ ቀጥለው 81ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልራህማን መሐመድ በቀኝ መስመር ገብቶ መሬት ለመሬት መትቶ በማስቆጠር ግብ አስገኝቶላቸው እንዲሁም 90ኛው ደቂቃ ላይ ጄሮም ፊሊፕ በራሱ ጥረት ግብ ጠባቂውንም አታሎ በማለፍ በማስቆጠር ጨዋታው 3ለ2 እንዲጠናቀቅ አድርጎል።

