ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ31ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ31ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች

ሸገር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በ37 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሸገር ከተማ ዛሬ በሜዳው የሊጉን መሪ ሲያስተናግድ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት የሚያስችል ነጥብ ለማግኘት ነው። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሦስቱን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ነጥብ የማስጠበቅ ችሎታ እንዳለው ቢያሳይም ድል የማድረግ ክፍተቱ ግን በደረጃው ከፍ እንዳይል እንቅፋት ሆኖበታል። ዛሬም የ+1 የግብ ልዩነት ያለውን የተከላካይ ክፍሉን አጥብቆ በመያዝ ከመሪው ነጥብ ለመንጠቅ ይገባል።

በ55 ነጥብ የሊጉን አናት የተቆጣጠረው ሲዳማ ቡና ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን የደረሰበት የ1 ለ 0 ሽንፈት የፈጠረበትን ጫና ለመቀነስ ዛሬ ወደ ድል መመለስ ግዴታው ነው። በሊጉ 18 ግቦችን ብቻ ያስተናገደው በያሬድ ባየ የሚመራው ጠንካራው የተከላካይ ክፍላቸው ዛሬም ዋነኛ መሣሪያቸው ነው። መሪዎቹ ከታች በ6 ነጥብ ልዩነት እየተከታተላቸው ካለው መቻል ለመራቅ ዛሬ የፊት መስመራቸው ላይ የሚታየውን የግብ ድርቀት ቀርፈው እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በጨዋታውም ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

የሲዳማ ቡናን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ቡድኑ ከመድን ጋር ባደረገው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣው ደግፌ አለሙ ለዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን ሰምተናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ባህር ዳር ከተማዎች በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ40 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋሉ። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ተለዋዋጭ አቋም ቢያሳይም (ሁለት ድል፣ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት) ባለፈው ሳምንት በደርቢ ጨዋታ ፋሲል ከነማን 2 ለ 0 በማሸነፍ ትልቅ መነቃቃት ላይ ይገኛሉ። የቡድኑ መልካም ጎን በተለይ የተከላካይ ክፍሉ መረጋጋት ሲሆን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ ግብ አለማስተናገዳቸው ለዛሬው ጨዋታ በራስ መተማመን ይሰጣቸዋል። ዛሬም ይህንን ጠንካራ የተከላካይ መስመር ይዘው በመግባትና የፊት መስመሩን ውጤታማነት በማስቀጠል ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ይጫወታሉ።

በሌላ በኩል ወልዋሎ አዲግራት በ35 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል እያደረገ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ድልና ሦስት ሽንፈቶችን ያስመዘገበ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በነገሌ አርሲ 2 ለ 1 መሸነፉ የዛሬውን ጨዋታ የሞት ሽረት ያደርገዋል። የወልዋሎ ደካማ ጎን የመከላከል ትኩረት ማጣትና ወጥ የሆነ አቋም አለማሳየቱ ሲሆን በተቃራኒው እንደ ቡና እና ንግድ ባንክ ያሉ ጠንካራ ቡድኖችን ማሸነፋቸው ለማንኛውም ቡድን አደገኛ ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ ያሳያል። ለዛሬው ጨዋታ ካለፉት ሽንፈቶች ተምረው በመከላከል ላይ ጥንቃቄ በማድረግና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን በመጠቀም ነጥብ ይዞ ለመውጣት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ሲገናኙ ባህርዳር ከተማ 2 ወልዋሎ ደግሞ 1 ጨዋታ አሸንፈው በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ባህርዳር ከተማ 4 ወልዋሎ ደግሞ 1 ግብ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ዓ.ም ጨዋታ አልተካተተም)

ባህር ዳር ከተማዎች መሳይ አገኘሁን በቅጣት እንዲሁም ማን ያዘዋል ካሳን በጉዳት ለዛሬው ጨዋታ አያገኙም። ወልዋሎዎች ብሩክ እንዳለና ኪሩቤል ወንድሙን በጉዳት ፍሬው ሰለሞን እና ሙሉዓለም መስፍንን ደግሞ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።

አርባምንጭ ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ በ28 ነጥብ 20ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች በሊጉ መቆያ ተስፋቸውን ለማለምለም ዛሬ የግድ ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። ባለፈው ሳምንት መቐለን 2 ለ 0 በማሸነፍ ትልቅ መነቃቃት ውስጥ የገቡት አዞዎቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በድምሩ 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ ካለባቸው ጫና ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። የቡድኑ መልካም ጎን በተለይ ግብ ጠባቂውና የተከላካይ ክፍሉ ከወትሮው በተሻለ መረጋጋታቸው ሲሆን ዛሬም ይህንን መከላከያ መነሻ በማድረግና የፊት መስመሩን ውጤታማነት ማስቀጠል ከቻሉ ወሳኝ ሶስት ነጥብ የማግኘት ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል።

በተቃራኒው ወላይታ ድቻ በ38 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የዛሬው ጨዋታውን ያደርጋል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ድሎችንና አንድ አቻ በማስመዝገብ በአስደናቂ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል ባለፈው ሳምንትም ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 ማሸነፋቸው ለዛሬው ፍልሚያ በራስ መተማመናቸውን ከፍ አድርጎታል። የጦና ንቦቹ ጠንካራ ጎን የቡድን ስራቸውና በተለይ በመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚን የመፈተን ብቃታቸው ቢሆንም አልፎ አልፎ በትኩረት ማጣት ግቦችን ማስተናገዳቸው እንደ ደካማ ጎን ይነሳል። ዛሬም ይህንን ወጥ አቋማቸውን አስቀጥለው በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ መካከለኛው ክፍል ከፍ ለማለት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች 17 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 10 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ወላይታ ድቻዎች 5 እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ 2 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

አርባምንጭ ከተማ በጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዞ ለዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ይቀርባል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከነማ

በ42 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት  ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሳምንታት በፊት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ጥሩ ጉዞ ላይ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች (በተለይ ባለፈው ሳምንት በሽረ 1 ለ 0 መሸነፉ) በውጤት ረገድ ወደ ኋላ እንዲል አድርጎታል። የኤሌክትሪክ መልካም ጎን ጥሩ አቅም ያላቸው ወጣቶችን የያዘና ኳስን መስርቶ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን መሆኑ ነው ሆኖም በወሳኝ ሰዓት ግብ የማስቆጠር ችግር ያለባቸው ሲሆን ይህም ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ የቤት ስራ ይሆንባቸዋል። ዛሬም ይህንን ድክመታቸውን በማረም ወደ ድል ጎዳና ለመመለስ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፋሲል ከነማ በ43 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች 7 ነጥብ በመሰብሰብ ግማሽ በግማሽ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል። የቡድኑ መልካም ጎን የታክቲክ ዲሲፕሊንና ተጋጣሚን ተጭኖ የመጫወት ብቃቱ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በጎረቤቱ ባህር ዳር ከነማ 2 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው። በመሆኑም ዛሬ ከደርቢ ሽንፈቱ አገግሞ ወደ ድል ለመመለስ የተከላካይ መስመር ትኩረቱን መጠበቅና የሚፈጠሩ ዕድሎችን ወደ ግብነት መለወጥ ይኖርበታል። ዛሬም ይህንን የታክቲክ ብልጫውን ተጠቅሞ ለደጋፊው የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ 6 ጊዜ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጎል ረገድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 12 ፋሲል ከነማ ደግሞ 13 ግቦች አስቆጥረዋል።

ፋሲል ከነማዎች የረጅም ጊዜ ጉዳት ካስተናገደው አምሳሉ ጥላሁን በስተቀር ሁሉም ተጫዋቾች ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።