በአዲስ አበባ በተደረጉ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ ምዓም አናበስትን ነብሮቹ ደግሞ ሐይቆቹን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸነፉ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቐለ 70 እንደርታ
የጨዋታው ሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፈረሰኞችን ከምዓም አናብስት በማገናኘት ጅማሮውን አድርጓል። የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተለያየ መልክ ያለው ፉክክር የታየበት ሲሆን ምዓም አናብስት ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ረገድ መጠነኛ ብልጫ ይዘው ቢታዩም ወደ ግብ ክልል ደርሰው አደጋ መፍጠር አልቻሉም።
ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በመፍጠር የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት ፈረሰኞቹ ሀብታሙ ጉልላት በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች እንዲሁም ተገኑ ተሾመ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ሞክሮ ባልተጠቀመበት ሙከራዎች የግብ አጋጣሚዎች ፈጥረዋል። አጋማሹም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ምዓም አናብስት አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ የቻሉበት ቢሆንም የግብ አጋጣሚዎች መፍጠር አልቻሉም። እንዲሁም 83ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ተስፋዬ ብሩክ አለማየሁ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶባቸው ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።

ፈረሰኞች በበኩላቸው በአጋማሹ ያደረጉት የግብ ፍለጋ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውም መምራት ጀምረዋል። 90ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ከድር አጥቂው ቧይ ኳይት ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎ በመጨረሻ ደቂቃ ፈረሰኞቹን አሸናፊ አድርጓቸው ጨዋታው ተቋጭቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ
በሀዲያ ሆሳዕና እና በሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ሁለተኛው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝና ብርቱ ፉክክር የታየበት ነበር። የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ነብሮቹ የተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደር የቻሉ ሲሆን እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫም ሙከራዎችን አድርገዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ለአንድ ተቀባብለው ኢዮብ አለማየሁ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ የተቆጣጠረበት፣ ፀጋዓብ ግዛው ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂውን የፈተነ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲጠቀስ የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ሄኖክ አርፍጮ ከርቀት መትቶ ለጥቂት ከፍ ብሎ ያለፈበት ሙከራም ይጠቀሳል።
በሐይቆቹ በኩልም ብሩክ ታደለ ከሳጥን ውጪ መቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ያወጣበት እንዲሁም ብሩክ ያሬድ ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ለመቆጣጠር ሲጥር ያመለጠው ኢላማውን የጠበቀ ሌላኛው ሙከራ የሚጠቀስ ሲሆን አጋማሹም በነብሮቹ በላይነት ተገባዶ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በጥሩ ፉክክር ጋር በተመለሰው በሁለተኛው አጋማሽ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመውጣት ውጤት እጅጉን ሲፈልጉ የነበሩት ነብሮቹ ግብ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ቆይተው 64ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማው ኳስ ተጨራርፎ የሐይቆቹ ተመላለሽ ተከላካይ ፍቃደስላሴ ደሳለኝ በእጁ ሲነካው ለኳስ ቅርብ የነበሩት የእለቱ ዋና ዳኛ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው ሄኖክ አርፊጮ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ሐይቆቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ እስከመጨረሻው ደቂቃ ቢታገሉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ነብሮቹ በሄኖክ አርፊጮ ብቸኛ ግብ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

