ሪፖርት| አዳማ ከተማዎች ወሳኝ ድል ሲቀዳጁ ኢትዮጵያ ቡና እና መቻል  ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| አዳማ ከተማዎች ወሳኝ ድል ሲቀዳጁ ኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ነጥብ ተጋርተዋል


አዳማ ከተማዎች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ሲታረቁ መቻል ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበትን ዕድል አባክኗል

አዳማ ከተማ ከ ሽረ ምድረ ገነት

አዳማ ከተማዎች ገና ከጅማሮው የጨዋታውን ብልጫ በመውሰድ ባሳዩት አስደናቂ እንቅስቃሴ መሪ ለመሆን የፈጀባቸው ዘጠኝ ደቂቃዎችን ብቻ ነበር። አማካዩ ሃይደር ሸረፋ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውና ድንቅ በሆነ ሁኔታ መረብ ላይ ያረፈው ኳስ አዳማዎችን ገና በጊዜ መሪ ማድረግ የቻለች ድንቅ ግብ ነበረች።

ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በ25ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል። አቤኔዘር ሲሳይ ድንቅ በሆነ እይታ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ቢንያም አይተን በጥሩ ብቃት ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ይህም አዳማዎች በጨዋታው ላይ ያላቸውን የበላይነት ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ረድቷቸዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ሲቀሩ የምድረ ገነት ሽረ ተከላካይ ፀጋአብ ዮሐንስ በፈጸመው ጥፋት በዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይህ ክስተት ቀድሞውኑ በውጤት ለተበለጡት ምድረ ገነት ሽረዎች የቁጥር መጉደሉንም ጨምሮ እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሽረዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም አዳማዎች በ59ኛው ደቂቃ ሶስተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው አብዱልከሪም መሐመድ በጥሩ ዕይታ ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ሳኒ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም አቤነዘር ሲሳይ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግብነት በመቀየር የድሉን ዋስትና አረጋግጧል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ዳንኤል ዳርጌ ለሽረ፣ ቢንያም አይተን ደግሞ ለአዳማ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጨዋታው በአዳማ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ውጤት አዳማ ከተማዎች ካለፉት ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ድል ጎዳና የተመለሱበትን ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ መቻል

ጨዋታው ገና ከጅማሮው በሁለቱም በኩል በሚሰነዘሩ ፈጣን ጥቃቶች የታጀበ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በቢንያም ጌታቸው አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ መቻሎች በበኩላቸው በኮሊንስ ኮፊ እና በአብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት የቡናን ግብ ደጋግመው ፈትሽዋል። ይሁን እንጂ የግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም ንቁነትና የግቡ አግዳሚ መቻሎችን ግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።

በ16ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር አዳሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ቢንያም ጌታቸው በግንባሩ በመግጨት ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሆኖም የቡናማዎቹ መሪነት የቆየው ለአምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር መቻሎች በጥሩ ሪትም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጭነው በመግባት የአቻነት ግባቸውን አግኝተዋል። ብሩክ ማርቆስ በሳጥን ውስጥ የተፈጠረውን ዕድል ተጠቅሞ ኳሷን መረብ ላይ በማሳረፍ መቻሎችን ወደ ጨዋታው መልሷል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በ87ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች የፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም በረከት ደስታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም መልሶበታል። ይህም መቻሎች ነጥባቸውን ከመሪው ጋር ለማጥበብ የነበራቸውን ወርቃማ ዕድል እንዲያባክኑ አድርጓቸዋል ጨዋታውም በ 1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል።