👉 “ከድካም ከረጅም መንገድ ተጉዘው ነው ልጆቻችን የመጡት…”
👉 “ጨዋታው አቅማችንን እንድናይ ለቀጣይ ፕላናችን ብዙ ነገር ያግዘናል።”
👉 “የወዳጅነት ጨዋታዎች ስናገኝ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
ከዩጋንዳ ጋር ከተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣርያውን ከዛምቢያ ጋር ሰኔ 27 እና ሐምሌ 5 ቀን እንደሚያካሂድ ይታወቃል። ለነዚህ ጨዋታዎችም አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ለ25 ተጫዋቾች ማክሰኞ ጥሪ አድርገው ትናንት ተጠናቀው በመግባት ዛሬ ረፋድ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር አድርገው 3-3 አቻ በሆነ ውጤት አጠናቀዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ከመገናኛ ብዙኀን ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
ስለ ጨዋታው…?
“እንደነዚህ ያሉ ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች ስናገኝ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። ከምስራቅ አፍሪካ ካሉት ጥሩ ቡድን ከሚባለው ዩጋንዳ ጋር መጫወታችን ጥሩ ነው። ቡድናችን ስብስብ ትናንት ነው እስከ ምሽት አምስት ሰዓት የገቡት። ጨዋታው አቅማችንን እንድናይ ለቀጣይ ፕላናችን ብዙ ነገር ያግዘናል።
ስለ ውጤቱ…?
“የምንጠብቀው ውጤት ነው። እንዳውም ከጠበቅነው በላይ ነው። ከድካም ከረጅም መንገድ ተጉዘው ነው ልጆቻችን የመጡት የሚችሉትን እንቅስቃሴ አድርገዋል። እንቅስቃሴውም በብዙ መሥራት እንዳለብን ማሳያ ነው። ዛምብያ ጠንካራ ተጋጣሚያችን ነው። ቢያንስ ከዩጋንዳ ጋር ጨዋታ ማድረጋችን ጥሩ ነው። ነገ ከነገ ወድያ ሌላ ተመሳሳይ ጨዋታ ብናገኝ የበለጠ የተሻለ ነው።
የወዳጅነት ጨዋታው ጊዜ እና ወቅቱን የጠበቀ ነው ?
“በእኛ ሀገር ደረጃ ተጫዋቾቻችን ራሳቸውን ስለማያዘጋጁ፣ ከጨዋታ ስለ ራቁ ነው እንጂ እንደነዚህ ያሉ ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው። ብዙ ነገሮች ለማየት ይረዳናል ሊበረታቱ ይገባል። ጨዋታዎች መማርያ ናቸው ተጫዋቾችም ራሳቸውን እንዲያዩ ይረዳል።

