👉 “ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ቢጠናቀቅም እኛ ማሸነፍ ይገባን የነበረ ጨዋታ እንደነበረ አስባለሁ።”
👉 “ድሬዳዋ እጅግ ውብ ቦታ ናት ህዝቡም ቢሆን እጅግ በጣም ደግ እና ተወዳጅ ነው። ብቸኛው ፈተና ሙቀቱ ብቻ ነው።”
👉 “ስታዲየሙ እጅግ በጣም ጥሩ ከመሆኑ የተነሳ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ጭምር ማስተናገድ የሚችል ነው።”

በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በማላዊ ብሔራዊ ቡድን የተደረገው የኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታ መካከል 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ካልሲቶ ፓሱዋ የሰጡትን ድህረ-ጨዋታ አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
“ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ቢጠናቀቅም እኛ ማሸነፍ ይገባን የነበረ ጨዋታ እንደነበረ አስባለሁ። ሆኖም ግን በተጫዋቾቻችን ላይ በታየው መዘናጋት ምክንያት ሳይሳካልን ቀርቷል። በዚህ የላቀ የእግር ኳስ ደረጃ ላይ ስህተቶችን መፈጸም የለብህም። በአንድ ግብ ብቻ ጨዋታን ማሸነፍ ይቻላል ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ቅዳሜ ዕለት ያደረግነው የመጀመሪያው ጨዋታ ነው ኢትዮጵያ 1 ለ 0 አሸንፋ ግቧን አስጠብቃ ወጥታለች። አሁን ደግሞ በተገላቢጦሹ እኛ እየመራን በአጋማሹ ማጠናቀቂያ ላይ ግብ አስተናግደናል። ስለዚህ በዚህ ደረጃ እግር ኳስ እንዴት መጫወት እንዳለብን ለልጆቻችን ገና ብዙ ማስተማር እና ማበረታታት ይኖርብናል።”
“በጨዋታው ላይ ያስተዋልኩት ሌላው ክፍተት ተጋጣሚያችን ከፍተኛ ጫና በሚፈጥርብን ወቅት ከዚያ ጫና ወጥቶ ኳስን መስርቶ መጫወት ላይ ክፍተቶች ነበሩብን። ስለዚህ ይበልጥ ጠንካራ ለመሆን በዚህ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።”
“ድሬዳዋ እጅግ ውብ ቦታ ናት! ብቸኛው ፈተና ሙቀቱ ብቻ ነው። ሙቀቱ በእጅጉ ቢለበልበንም ከተማዋ ግን በጣም ደስ የምትል ናት። ወደፊት እዚህ ብዙ ጨዋታዎችን የማድረግ ዕድል የምናገኝ ከሆነ በደስታ ተመልሰን እንመጣለን። ህዝቡም ቢሆን እጅግ በጣም ደግ እና ተወዳጅ ነው።”
“ከጨዋታው ያገኘናቸው አዎንታዊ ጎኖች አሉ፤ አንደኛው አሁን ላይ ቢያንስ ወደ ፊት በመሄድ ረገድ መሻሻሎች አሳይተናል።
“ስታዲየሙ እጅግ በጣም አሪፍ እና ጥሩ ስታዲየም ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ስታዲየም ለምን ያህል ጊዜ እንደተጠቀመችበት ባላውቅም ስታዲየሙ እጅግ በጣም አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ጭምር ማስተናገድ ይችላል።”

