ወልዋሎዎች ቅሬታ አቀረቡ

ወልዋሎዎች ቅሬታ አቀረቡ

ቢጫዎቹ ከጨዋታ ውጤት ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን አስምተው የፍፃሜው ጨዋታ እንዲራዘምም ጥያቄ አቅርበዋል

በ37ኛ ሳምንት በሰመረ ሀፍታይ ብቸኛ ጎል አርባምንጭ ከተማን ማሸነፍ የቻሉት ወልዋሎዎች በትናንትናው እለት በኢትዮጵያ መድን እና ሽረ ምድረ ገነት መካከል በተካሄደው ጨዋታ ዙርያ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ባገኘችው መረጃ መሰረት ወልዋሎዎች ኢትዮጵያ መድን ከአቅም በታች ተጫውተዋል የሚል ቅሬታ እንዳላቸው እና ቅሬታቸውም ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እንዳቀረቡ አረጋግጠናል።

ክለቡ በትናንትናው ጨዋታ የመድን ዋና አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ መገኘታቸው እንዲሁም ከጨዋታ በፊት እና በኋላ በቀጥታ ስርጭት ወቅት ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ጋር ቃለ ምልልስ አለማድረጋቸው ይህንንም በምክትል አሰልጣኙ በኩል ማስፈፀማቸው ጥርጣሬያቸውን ከፍ እንዳደረገውም በደብዳቤው ጠቅሷል።

ክለቡ በዛሬው እለት በኢሜይል በላከው ደብዳቤ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ የጠየቀ ሲሆን ቀሪ የ37ኛ እና 38ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመሰል ጥፋቶች እንዳይፈፀሙ በጥንቃቄ መታየት እንዳለባቸው አሳስቧል። ከዚህ በተጨማሪም ከሲዳማ ቡና ጋር የሚያደርገውን የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታም በመርሐ ግብር መደራረብ ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጥያቄ አቅርቧል።