በ37ኛ ሳምንት እርስበርስ የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ በጨዋታው ላይ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ መጠነኛ ግጭት ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

በአ/ሳ/ቴ/ዩ/ ስታዲየም በተካሄደው የ37ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጹም ጥላሁን ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማን 1ለ0 መርታቱ ይታወሳል። በዚሁ ጨዋታ ላይ በደጋፊዎች ተፈጥረዋል ላላቸው ችግሮች አወዳዳሪው አካል ቅጣት አስተላልፏል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የኦቢኤን ባክግራውንድ ቢልቦርድ በመሰበሩ አዲስ እንዲያሠሩ ወይም ድርጅቱ አሠርቶ የሚያቀርበውን ዋጋ እንዲከፍሉ ፣ በግራ ጥላፎቅ የነበሩ ደጋፊዎች ወደ ፋሲል ደጋፊዎች ቁሳቁሶችን በመወርወር እና ከሜዳ ውጪም ደጋፊ ላይ ጉዳት ያደረሰ ብጥብጥ በመፍጠራቸው ክለቡ 50ሺህ ብር ቅጣት ፤ ደጋፊዎች ደግሞ የመጨረሻውን የክለባቸው ጨዋታ ስታዲየም ገብተው እንዳይመለከቱ ሲወሰን
በፋሲል ከነማ በኩል በቀኝ ጥላፎቅ የነበሩ ደጋፊዎች ወደ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ቁሳቁሶችን በመወርወር በመወርወር እና ከሜዳ ውጪም ደጋፊ ላይ ጉዳት ያደረሰ ብጥብጥ በመፍጠራቸው ክለቡ 50ሺህ ብር ቅጣት ፤ ደጋፊዎች ደግሞ የመጨረሻውን የክለባቸው ጨዋታ ስታዲየም ገብተው እንዳይመለከቱ ተወስኗል።

