በትናንትናው ዕለት ጫማውን ከሰቀለው መስዑድ መሐመድ ጋር የተደረገ ቆይታ

በትናንትናው ዕለት ጫማውን ከሰቀለው መስዑድ መሐመድ ጋር የተደረገ ቆይታ

👉 “ትክክለኛው ሰዓት ላይ ትክክለኛውን ውሳኔ ወስኛለሁ ብዬ አስባለሁ”

👉 “ጊዜው በጣም ነው የሚሮጠው በተለይ እግርኳስ ላይ ሲሆን”

👉 “በስልጠናው የሆነ ነገር ለሀገሬ አበረክታለው ብየ አስባለሁ።”

👉 “እንዲህ ያሉ ነገሮችን መናገር ስሜታዊ ያደርጋል።”

በትናንትናው ዕለት ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ጫማውን መስቀሉን ይፋ ካደረገው ከአመለ ሸጋው መስዑድ መሐመድ ጋር የተደረገ ቆይታ።

ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮ ኤሌክትሪክ እስከ ዋናው ቡድን በመጫዋት የእግርኳስ ሕይወቱን በክለብ ደረጃ የጀመረው መስዑድ መሐመድ በመቀጠል ኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ የመጀመርያ የሊጉን ዋንጫ እንዲያሳካ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ተጫዋች ከሆነ በኋላ ጅማ አባጅፋር ፣ አዳማ ከተማ ፣ ሰበታ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ቆይታ ያደረገው ባለ ብዙ ልምዱ አማካይ መስዑድ መሐመድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ስኬታማ ቆይታን አድርጓል። አመለ ሸጋው መስዑድ በትናንትናው ዕለት በይፋ ጫማውን መስቀሉን በማህበራዊ ገፁ ይፋ ያደረገ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ስንብቱን አስመልክቶ ላቀረበችለት ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል።

ያለፉት ሃያ ዓመታት እንዴት አለፉ?

“ያሳለፍኩትን ሃያ ዓመታት እንደ ትናንትና ነው ሁሉን የማስታውሰው እግርኳስን ከታዳጊነት እስካሁን ጊዜው በጣም ነው የሚሮጠው በተለይ እግርኳስ ላይ ሲሆን ይገርማል። የምትወደውን ሥራ ስለምትሠራ ጊዜው በጣም ነው የሚሮጠው ድንገት አንጋፋ ትባላለህ ያው ሂደቱን ጠብቀህ ከእግርኳስ ትወጣለህ ። ያለፉት ጊዜያት ብዙ መውደቅ መነሳት የነበረው ነው። ነገር ግን የምትወደው ነገር ሲሆን ሁሉን ነገር እየቻልክ የምታሳልፈው ጊዜ ነው። ያው በዚህ ሰዓት ላይ እንዲህ ያሉ ነገሮችን መናገር ስሜታዊ ያደርጋል። ነገር ግን በጣም ነው ጊዜው የሚፈጥነው የምትወደውን ነገር ስትሠራ ያው የሆነውን መቀበል ነው።”

አቋምን ጠብቆ ከስነምግባር ጋር ለመዝለቅህ ምክንያት?

“በልጅነቴ ያገኘዋቸው አሰልጣኞች ውለታ አለብኝ ብየ አስባለሁ። አሰልጣኝ ማርቆስ እና አሰልጣኝ መርሻ በደንብ ነው በልጅነታችን መስመር ያስያዙን እግርኳስን ብቻ ሳይሆን የሕይወት መንገዳችንን እንድናውቅ በደንብ ነው ቀርፀው ያሳደጉን እና እነዚህ በልጅነት ያገኘናቸው አሰልጣኞች ናቸው ሁሉን ነገር መስመር አስያዙኝ ብየ የማስበው።”

እግርኳስን ለማቆም ከውሳኔ ያደረሰህ ምክንያት?

“ከበቂ በላይ ተጫውቻለውሁ ፣ ሁልጊዜም ሳስበው የነበረ ነገር ነው። ያው እያሰብከው ብትቆይም መወሰኑ እንደማሰብ ቀላል አይደለም። ግን የግድ መሆን አለበት ዛሬ ባይሆን ነገ መሆኑ አይቀርም። ትክክለኛው ሰዓት ላይ ትክክለኛ ውሳኔ ወስኛለው ብዬ አስባለሁ።”

በቀጣይ ወደ ስልጠናው ትገባለህ?

“የካፍ ቢ ዲፕሎማ ይዣለው። በቀጣይ ልጆች ላይ ወይም በትልቅ ደረጃ አሰለጥናለሁ ብየ አስባለሁ ፤ የሕይወቴን አብዛኛው ዘመን እግርኳስ ላይ ነው ያሳለፍኩት በቀጣይም በስልጠናው የሆነ ነገር ለሀገሬ አበረክታለሁ ብየ አስባለሁ። እዚህ ሙያ ላይ እቆያለሁ ብዬ አስባለሁ።”

በመጨረሻም ምስጋና?

“ከልጅነት ጀምሮ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኝ ማርቆስ አሰልጣኝ መርሻ ፣ ኤልያስ ጁሀርን ጨምሮ በብሔራዊ ቡድን በክለብ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች ሁሉም ማመስገን እፈልጋለሁ። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ፣ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ፣ ጋሽ ሰውነት ቢሻው በጣም በጣም በብዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላሰለጠነኝ አሰልጣኝ የለም። የእነዚህን ሁሉ ውለታ ከፍዬ የምጨርሰው አይደለም። በተረፈ ደግሞ እግርኳስ አሰልጣኝ ሳይሆን እግርኳስን የምረዳበት መንገድ ቀይሮልኛል ብዬ የማስበው በእግርኳስ ብቻ ሳይሆን በሕይወት መንገድ  አስተምሮኛል ብየ የማስበው ተድላ በላቸውን ማመስገን እፈልጋለሁ።”