በጣምራ የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ታምራት ኢያሱ ከግብፁ ክለብ ጥያቄ ቀረበለት።

በውድድር ዓመቱ አጋማሽ አርባምንጭ ከተማን ለቆ ወደ ዐፄዎቹ የተቀላቀለው እና ከናትናኤል ዳንኤል ጋር በጣምራ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር የተቀዳጀው ታምራት ኢያሱ ከግብፁ ሞደርን ስፖርት ክለብ የዝውውር ጥያቄ ቀርቦለት ክለቡ ፋሲል ከነማም በዛሬው ዕለት ምላሽ እንደሰጠ ይሄንን ዕድል ካመቻቸው የተጫዋቹ ተወካይ አዛርያስ ተስፋፅዮን አረጋግጠናል።
ከቀናት በፊት በዕለተ ማክሰኞ ሐምሌ 21 የሙከራ ዕድል እንዳመቻቸና የሙከራ ጊዜው በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀ ተጫዋቹን የማዘዋወር ፍላጎት እንዳለው ለተጫዋቹ ባለቤት ፋሲል ከነማ በደብዳቤ የገለፀው የግብፁ ክለብ በዛሬው ዕለት ከዐፄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶታል። በዚህ መሰረት ፋሲል ከነማዎች ክለቡ ያቀረበላቸው የሙከራና የዝውውር ጥያቄ እንዳልተቀበሉት በመግለፅ በቀጣይ ጊዜ ከክለቡ ጋር አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

